“የትግራይ ክልል ክለቦች ወደ ውድድር እንዲመለሱ እንፈልጋለን” – የስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር ኤሊያስ ሽኩር

ሦስቱን የትግራይ ክልል ክለቦችን በተመለከተ የኢፌዲሪ ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ኤሊያስ ሽኩር አስተያየት ሰጥተዋል።

የዘንድሮ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የውድድር ዘመን ከመጀመሩ አስቀድሞ በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል በተነሳው የፀጥታ ችግር ምክንያት በውድድሩ ያልተሳተፉት መቐለ 70 እንደርታ፣ ወልዋሎ ዓ/ዩ እና ስሑል ሽረ በቀጣዩ ዓመት (2014) ወደ ሊጉ የመመለሳቸው ነገር እስካሁን መልስ ሳያገኝ ቀርቷል። እርግጥ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር ክለቦቹ እስከ ሐምሌ 15 ድረስ ምዝገባ ማድረግ እንደሚችሉ ቀነ ገደብ ቢሰጥም የክለቦቹ የመሳተፍ ጉዳይ የለየለት የመጨረሻ መልስ ሳያግኝ ቀጥሏል። የኢትዮጵያ እግርኳስ የበላይ አካል የሆነው የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽንም ሦስቱ ክለቦች ወደ ውድድር የሚመለሱበትን መንገድ ለማመቻቸት ከአመራሮቹ ጋር ንግግር እያደረገ ይገኛል። ይህ በእንዲህ እንዳለ በብሔራዊ ስታዲየም የግንባታ ሂደት ዙርያ መግለጫ የሰጡት የኢፌድሪ ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ኤሊያስ ሽኩር እግረ-መንገድ በጉዳዩ ዙርያ ጥያቄ ቀርቦላቸው ሀሳብ ሰጥተዋል።

“የትግራይ ክልል ክለቦች ወደ ውድድር እንዲመለሱ እንፈልጋለን። መምጣት እና መወዳደር አለባቸው። የክለቦቹ አመራሮች ከኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ጋር እየተወያዩ እንደሆነ እናውቃለን። ይሄንን የቤት ስራም የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ነው መውሰድ ያለበት። እንዳልኩት ውይይቱ ስለተጀመረ የሚመጡ ነገሮችን አብረን እናያለን። ክለቦቹም ጊዜ ስጡን እንዳሉ ሰምተናል። እንዳልኩት ይሄንን ጉዳይ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ነው የሚሰራው። እኛ ግንኙነታችን ከኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ጋር ነው። ይህ ማለት ግን ሌላ ምንም ስራ አንሰራም ማለት አይደለም። ሦስቱ ክለቦች ወደ ውድድር የሚመለሱበትን መንገድ እኛም እናስተካክላለን።”

ክቡር ኮሚሽነሩ ጨምረውም ተቋማቸው ከትግራይ ክልል ስፖርት ኮሚሽን ጋር ያለውን ግንኙነት በተመለከተ ተከታዩን ብለዋል።

“ከክልሉ (ትግራይ) ስፖርት ኮሚሽን ጋር እንደ ማንኛውም ክልል ግንኙነት አለን። ሌሎቹን ክልሎች በምናገኛቸው መልኩ እነርሱንም እናገኛለን። በቅርቡ እንደውም ድጋፍ አድርገንላቸዋል። ድጋፉ የገንዘብ፣ የቁሳቁስ እንዲሁም የቴክኒክ ድጋፍ ነው። በቀጣይም የክልሉን የስፖርት ኮሚሽን ለማገዝ እንሞክራለን።” ብለዋል