“የአክሲዮን ማኅበሩ ስም በዚህ ጉዳይ በመነሳቱ በጣም አዝነናል” – አቶ ክፍሌ ሠይፈ

የረፋዱ ጨዋታ የፕሪምየር ሊጉ የበላይ ለስታዲየም ሰራተኞች መከፈል የነበረበትን ገንዘብ ባለመክፈሉ ነው የተራዘመው?

ሦስቱ የትግራይ ክልል ክለቦች በሊጉ መሳተፋቸው ካልተረጋገጠ እነርሱን ለመተካት የሚደረገው ውድድር ዛሬ በሀዋሳ ዩኒቨርስቲ ስታዲየም ተጀምሯል። የውድድሩ የመክፈቻ ጨዋታ 3:00 ይደረጋል ተብሎ መርሐ-ግብር ቢወጣለትም የስታዲየሙ ሰራተኞች “የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ እዚህ ሲከናወን ያገለገልንበት ክፍያ በአክሲዮን ማኅበሩ አልተከፈለንም” ብለው ሁለቱን (ወልቂጤ ከተማ እና ጅማ አባጅፋር) የክለብ አባላት ወደ ስታዲየም አላስገባም ብለው የጨዋታው የመጀመሪያ ሰዓት ተስተጓጉላል። ይሄንን ጉዳይ በስፍራው የተከታተለው ባልደረባችን እንደታዘበው ከሆነ የሲዳማ ክልል በጉዳዩ ጣልቃ ቀብቶ ሰራተኞቹ እምቢታቸውን ትተው ክለቦቹ ወደ ሜዳ እንዲገቡ ተደርጓል። ይሄ ከሆነ በኋላ ደግሞ የመጫወቻ ሜዳው ሳር ለጨዋታ ዝግጁ ሳይሆን በመቅረቱ እንደ አዲስ ሜዳውን የማስተካከል ስራ (ሳር የማጨድ) መሰራት ተጀምሯል። ቀድሞ መሰራት የሚገባው ስራ አለመሰራቱን ተከትሎ ደግሞ ሜዳው እስኪስተካከል ደቂቃዎች ወስደው ጨዋታው ከተያዘለት ሰዓት አንድ ሰዓት ከሰላሳ ስምንት ደቂቃ እንዲራዘም ሆኗል።

በስታዲየሞቹ ሰራተኞች ሀሳብ እና በሜዳው ሳር አለመስተካከል (አለመታጨድ) የተራዘመው ጨዋታ በተባለው መልኩ ተጓቶ ቢደረግም “በጉዳዩ ውስጥ ስሜ ያለአግባብ ተነስቷል” ያለው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አክሲዮን ማኅበት በስራ አስኪያጁ አቶ ክፍሌ ሠይፈ በኩል ለዝግጅት ክፍላችን ተከታዩን ሀሳብ ሰጥቷል።

“የአክሲዮን ማኅበሩ ስም በዚህ ጉዳይ በመነሳቱ በጣም አዝነናል። ሲጀምር እኛ ያወዳደርነው ውድድር እና ይሄ ውድድር ይለያያል። ከአዲስ አበባ ጀምሮ ውድድር ባደረግንባቸው አምስቱም ከተሞች የጥበቃ የሚባል ክፍያ ከፍለን አናውቅም። ለጥበቃዎቹ ክፍያ ሊፈፅሙ የነበረው የሲዳማ ክልል ስፖርት ኮሚሽን ነው። እኛ ሜዳ ለሚያስተካክል፣ ለኳስ አቀባይ እና ለፅዳት ነው የምንከፍለው። እርሱንም በውላችን መሠረት። ሀዋሳ ላይ ላሉት ሦስቱም አካላት ደግሞ ክፍያውን ፈፅመናል። ውድድር ልክ እንደጨረስን የዳኛ እና የኮሚሽነሮችን ጨምሮ ሁሉንም ያለብንን ክፍያ ፈፅመናል።

“ጉዳዩ እንደተሰማ እኛ ውድድር በስታዲየሙ እንድናደርግ የፈቀደልንን አካል ደውዬ ጠይቄው ነበር። እኛ ገንዘብ እንዳለብንም ስጠይቀው እንደሌለብን ነግሮኛል። እንዳልኩት ተቋማችን ዘንድሮ ጠንካራ ስራ ከሰራበት አንዱ የክፍያ አፈፃፀም ጉዳይ ነው። የክፍያ ስርዓታችን በጣም የተሻለ ነው። ስለዚህ የተባለው ስህተት ነው። በእኛ በኩል ምንም ክፍተት የለም። ምንም አይነት ክፍያም የለብንም።”