የካፍ ቻምፒየንስ ሊግ የማጣሪያ ድልድል የሚወጣበት ቀን ታውቋል

በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ስምንት ክለቦችን በማሳተፍ የሚደረገው የሴቶች የቻምፒየንስ ሊግ የዞን የማጣሪያ ጨዋታዎች ድልድል የሚወጣበት ቀን ተገልጿል።

የአህጉሩን የሴቶች እግርኳስ ለማሳደግ የተለያዩ ሥራዎችን እየሰራ የሚገኘው ካፍ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የሴቶች ቻምፒየንስ ሊግ ውድድር ለማድረግ መወሰኑ ይታወቃል። በመጀመሪያው ውድድር ላይም ስምንት ክለቦች እንደሚሳተፉ የተገለፀ ሲሆን እነርሱን ለመለየት ደግሞ በየዞኑ የማጣሪያ ጨዋታዎች የሚደረጉ ይሆናል። የዘንድሮ የሴቶች ፕሪምየር ሊግ አሸናፊው እና በኬንያ አስተናጋጅነት በሚከናወነው የሴካፋ ዞን የማጣሪያ ውድድር ላይ ተሳትፎ የሚያደርገው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በበኩሉ ዘግይቶም ቢሆን ባሳለፍነው ዓርብ መቀመጫውን ደብረዘይት በማድረግ ለውድድሩ ዝግጅቱን ጀምሯል።

በስድስት የአፍሪካ ዞን በሚደረጉ ውድድሮች አሸናፊ የሚሆኑ ክለቦችን (ስድስት)፣ የውድድሩ አስተናጋጅ ግብፅ አንድ ክለብን እና የወቅቱ የሴቶች የአፍሪካ ዋንጫ አሸናፊ ከሆነ ሀገር የመጣ አንድ ክለብን በጠቅላላ ስምንት ክለቦች የሚሳተፉበት ዋናው ውድድር ከመጀመሩ በፊት ከዛሬ አንስቶ የየዞኖቹ የማጣሪያ ጨዋታዎች ድልድል እንደሚወጣ ተመላክቷል። በዚህም በዛሬው ዕለት የዋፉ ቢ ዞን የምድብ ድልድል የሚወጣ ይሆናል።

የሀገራችን ተወካይ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሚሳተፍበት የሴካፋ ዞን የማጣሪያ ድልድል ደግሞ ከነገ በስቲያ ረቡዕ እንደሚወጣ ተጠቁሟል። ካፍ እንዳስታወቀው ከሆነ በሴካፋ ዞን በሚደረገው ውድድር ላይ ፒ ቪ ፒ ቡየንዚ (ቡሩንዲ)፣ ኤፍ ኤ ዲ ክለብ (ጂቡቲ)፣ ንግድ ባንክ (ኢትዮጵያ)፣ ቪሂጋ ኩዊንስ (ኬንያ)፣ ሌዲ ዶቭስ (ዩጋንዳ)፣ ይ ጆይን ስታርስ (ደ.ሱዳን)፣ ሲምባ ኩዊንስ (ታንዛኒያ) እና ስካንድኔቪያን (ሩዋንዳ) እንደሚካፈሉ ተብራርቷል። በውድድሩ የሱማሊያ ክለብ እንደማይኖር ቀድሞ መገለፁ ሲታወስ ምናልባት በመረጃው ያልተካተቱት የኤርትራ እና ሱዳን ሀገር ክለቦችም እጣ ፈንታ በግልፅ እንዳለየ ለማወቅ ተችሏል።

የዞኑ (ሴካፋ) የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታዎች ከጁላይ 17 ወይም ከሐምሌ 10 ጀምሮ በኬንያ አስተናጋጅነት መከወን ይጀምራሉ።