ዋልያው ባህር ዳር ሲደርስ ደማቅ አቀባበል ተደርጎለታል

በሴካፋ ውድድር ላይ የሚካፈለው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ውድድሩ በሚደረግበት ባህር ዳር ከተማ ሲደርስ ደማቅ አቀባበል ተደርጎለታል።

ከ1926 ጀምሮ መደረግ የጀመረው የምስራቅ እና መካከለኛው የአፍሪካ ዋንጫ (ሴካፋ) ውድድር የ2021 የውድድር ዓመቱን የቀጠናው ፍልሚያ በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት ያከናውናል። በአሠልጣኝ ውበቱ አባተ የሚመራው የኢትዮጵያ ከ23 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድንም ለዚህ ውድድር ከሰኔ 4 ጀምሮ ዝግጅቱን ሲያደርግ ከርሟል። ልዑካኑም በአዲስ አበባ የሚያደርገውን የዝግጅት ምዕራፍ አገባዶ ውድድሩ ወደሚደረግበት ባህር ዳር ከተማ ረፋድ ላይ በሯል።

25 ተጫዋቾችን በመያዝ ወደ ባህር ያቀናው ስብስቡም 5 ሰዓት ሲል ባህር ዳር አየር ማረፊያ ደርሷል። ቡድኑ ከአውሮፕላን ሲወርድም በቅርቡ የኢትዮጵያ እግርኳስ ደጋፊዎች ማኅበር የአማራ ክልል ዋና አስተባባሪ ሆነው የተሾሙት አቶ እሱባለው ልይህ የአማራ ክልል የባህል እና ቱሪዝም ቢሮ ሀላፊ አቶ አብርሃምን እና የአማራ ክልል ስፖርት ኮሚሽን ሀላፊዎችን በመጋበዝ ለብሔራዊ ቡድኑ ደማቅ አቀባበል አድርገውላቸዋል። በማህበሩ አስተባባሪነት በአየር ማረፊያው የእንኳን ደህና መጣችው አቀባበል ከተደረገ በኋላም ልዑካኑ ወደሚያርፍበት ብሉናይል ሆቴል እና ሪዞርት (አቫንቲ ሆቴል) በሞተረኛ ትራፊኮች እና የስፖርት ቤተሰብ ታጅቦ መጓዙ ታውቋል።

በተያያዘ ዜና በአሠልጣኝ ውበቱ የሚመራው ቡድኑ ቀጣዮቹን ሦስት ሰዓታት እረፍት ካደረገ በኋላ 9:30 በባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም ልምምድ እንደሚሰራ ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል።