ፋሲል እና ቡና በአፍሪካ መድረክ በሜዳቸው የሚጫወቱበት ስታዲየም ታውቋል

በካፍ ቻምፒየንስ ሊግ እና ኮንፌዴሬሽን ካፕ የሚሳተፉት ፋሲል ከነማ እና ኢትዮጵያ ቡና የሜዳ ላይ ጨዋታቸውን የሚያደርጉበት ስታዲየም ታውቋል።

በዘንድሮ የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ አንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃን ይዘው ያጠናቀቁት ፋሲል ከነማ እና ኢትዮጵያ ቡና በ2021/22 የውድድር ዓመት ኢትዮጵያን በካፍ ቻምፒየንስ ሊግ እና ኮንፌዴሬሽን ካፕ እንደሚወክሉ ይታወቃል። ከቀናት በፊት የአፍሪካ እግርኳስ የበላይ አካል የሆነው ካፍ የመጀመሪያ ዙር የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታዎች ከጳጉሜ 5 ጀምሮ እንደሚደረጉ አስታውቆ ነበር። ዛሬ በተገኘ መረጃ ደግሞ በውድድሩ የሚካፈሉ ክለቦች በሜዳቸው የሚያደርጉትን ጨዋታ በየትኛው ስታዲየም እንደሚያደርጉ ተገልጿል።

በፓትሪክ ሞሴፔ የሚመራው ካፍ የአህጉሩን የክለቦች ውድድርን ጥራት ከፍ ለማድረግ አዳዲስ ህጎችን እያወጣ እንደሚገኝ ይታወቃል። ከወጡት ህጎች እና ደንቦች መካከል ደግሞ የካፍ ቻምፒየንስ ሊግ እና ኮንፌዴሬሽን ካፕ የግማሽ ፍፃሜ እና የፍፃሜ ጨዋታዎች እንዲሁም የካፍ ሱፐር ካፕ ጨዋታ በደረጃ- 1 (Category-1) ዝርዝር ውስጥ በተያዙ ስታዲየሞች እንዲደረጉ የሚያዘው ይገኝበታል። ደረጃ አራት (Category-4) መደብ ውስጥ ያሉ ስታዲየሞች ደግሞ የሴቶች ቻምፒየንስ ሊግ ጨዋታዎችን እንዲሁም በደረጃ ሦስት ስር የሚገኙ ስታዲየሞች ደግሞ የማጣሪያ (የቻምፒየንስ ሊግ እና ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ) እና የምድብ ጨዋታዎችን ብቻ እንዲያስተናግዱ አቅጣጫ ተቀምጧል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ በቻምፒየንስ ሊግ ውድድር ላይ የሚሳተፈው ፋሲል ከነማ እና ከአስር ዓመታት በኋላ ወደ አህጉራዊ ውድድሮች የተመለሰው ኢትዮጵያ ቡና የሜዳ ላይ ጨዋታቸውን በባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም እንደሚያደርጉ ተጠቁሟል።

በተያያዘ ከቡርኪናፋሶ፣ ብሩንዲ፣ መካከለኛው አፍሪካ፣ ቻድ፣ ኤርትራ፣ ጋምቢያ፣ ሌሴቶ፣ ናሚቢያ፣ ኒጀር፣ ሳዎ ቶሜ፣ ሴኔጋል፣ ሲሸልስ፣ ሴራሊዮን፣ ሶማሊያ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ኢስዋቲኒ እና ዛንዚባር የሚመጡ ክለቦች እስከ ሐምሌ 14 (ጁላይ 21) ድረስ በሀገራቸው የሚጫወቱበትን ስታዲየም ማፀደቅ ካልቻሉ በጎረቤት ሀገር ጨዋታቸውን እንደሚያደርጉ ተመላክቷል።

*በሁለቱ የአህጉሩ ውድድሮች የሚሳተፉ ክለቦች የሜዳ ላይ ጨዋታቸውን የሚያደርጉበትን ስታዲየም መቀየር ከፈለጉ እስከ ሐምሌ 14 ድረስ በቪድዮ የተቀረፀ የስታዲየሙን ገፅታ አባሪ በመላክ ለካፍ ሪፖርት እንዲያደርጉ ተገልጿል።