“ጀግኒት” የኢትዮጵያ ሴቶች የፉትሳል ውድድር ዛሬ አሸናፊውን አግኝቷል

ከሰኔ 2 ጀምሮ በስምንት ቡድኖች መካከል ሲደረግ የነበረው የሴቶች የፉትሳል ውድድር ዛሬ ፍፃሜውን አግኝቷል።

በሴቶች እግርኳስ ላይ ትኩረት ሰጥተው የሚሰሩት ትዕንግርት የሴቶች ስፖርት እና ልሳን የሴቶች ስፖርት በጥምረት እንስት እግርኳስ ተጫዋቾች ከውድድር መራቃቸውን ተከትሎ በግል ተነሳሽነታቸው የክረምት የፉትሳል ውድድር አዘጋጅተው እንደነበር ይታወቃል። ከሰኔ 2 ጀምሮ በኢትዮጵያ ወጣቶች እና ስፖርት አካዳሚ ሲካሄድ የቆየው ውድድርም ዛሬ ኢትዮጵያዊነትን እና ቴክ ኦፍ መኪና ቡድኖችን ለፍፃሜ አገናኝቷል። ከሁለቱ ቡድኖች የፍፃሜ ጨዋታ በፊት የሴቶች ክለብ አሠልጣኞች ለሁለት ተከፍለው አዝናኝ ጨዋታ አድርገዋል። በዋናው ፕሪምየር ሊግ እና በሁለተኛው ዲቪዚዮን የሚገኙ ክለብ አሠልጣኞች ተደባልቀው በተጫወቱበት አዝናኝ ጨዋታም ሰባት ጎሎች ተቆጥረው ተጠናቋል።

ከአሠልጣኞቹ ጨዋታ በኋላ የተደረገው የውድድሩ የፍፃሜ ጨዋታም እንደ አሠልጣኞቹ ጨዋታ አዝናኝ ሆኖ ተከናውኗል። ገና ከጅምሩ ግብ ማስተናገድ የጀመረው እና ድንቅ ግቦችን ሲያስመለክት የነበረው የኢትዮጵያዊነት እና ቴክ ኦፍ መኪና ጨዋታም በአጠቃላይ ስድስት ግቦች ተመዝግበውበት በቴክ ኦፍ መኪና ቡድን 4-2 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ጨዋታው ከተጠናቀቀ በኋላ በዕለቱ በክብር እንግድነት የተገኙት የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ባህሩ ጥላሁን፣ የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ዋና አሠልጣኝ ብርሃኑ ግዛው፣ ኢንስትራክተር ሠላም ዘርዓይ እና የኢትዮ ኤሌክትሪክ አሠልጣኝ መሠረት ማኒ (በአሠልጣኞች ጨዋታ ላይ ተጫውታለች) የሽልማት አሠጣጥ መርሐ-ግብሩ ከመከናወኑ በፊት ንግግር አድርገዋል። በክብር እንግድነት የተገኙት አራቱም ግለሰቦች በንግግራቸው የእንስት እግርኳስ ተጫዋቾችን የእረፍት ጊዜ በማየት ውድድሩን እንዲዘጋጅ ላደረጉት ዳዊት ሀብቴ እና ዳግም ዝናቡ ምስጋና አቅርበዋል። ግለሰቦቹ አክለውም ከዚህም በኋላ ሊጎች እስኪጀምሩ ድረስ ሌሎች መሰል የክረምት ውድድሮች ቢዘጋጁ ጥሩ እንደሆነ አውስተዋል። በተለይ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ባህሩ ተቋማቸው ፉትሳል እና ቢች-ሶከር በሚል ዘርፍ የማወዳደር እቅድ እንዳለው ነገር ግን ሥራዎች እየተሰሩ አለመሆኑን ገልፀው ይሄ ውድድር ለፌዴሬሽኑ ትልቅ የቤት ስራ እንዲወስድ እንዳደረገው አመላክተዋል። 

ከክብር እንግዶቹ ንግግር በኋላ በውድድሩ ለተሳተፉ ቡድኖች እና ውድድሩ በተሳካ ሁኔታ እንዲከወን ላስተባበሩ አካላት የምስጋና የምስክር ወረቀት አሠጣጥ ተከናውኗል። በመጨረሻም የውድድሩ አሸናፊ የሆኑት የቴክ ኦፍ መኪና የቡድን አባላት በአምበላቸው መዲና ዐወል አማካኝነት ከኢንስትራክተር ሠላም ዘርዓይ ዋንጫቸውን እና 18 ሺ ብር ተረክበዋል።

የውድድሩ አዘጋጅ ጋዜጠኛ ዳዊት ሀብቴ የኢትዮጵያ ወጣቶች እና ስፖርት አካዳሚ የሜዳ ትብብር ስላደረገለት ምስጋና አቅርቧል።