የፌዴሬሽኑ ጋዜጣዊ መግለጫ…

የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ዛሬ በፅሕፈት ቤቱ በሰጠው መግለጫ ዋነኛ አጀንዳው ከእስራኤል አቻው ጋር በፈፀመው ስምምነት ዙርያ ቢሆንም ስለ የሴካፋ መራዘምም ተገልጾበታል።

የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳይያስ ጂራ እና ዋና ጸሐፊ አቶ ባህሩ ጥላሁን በሰጡት መግለጫ ላይ ፌዴሬሽኑ ከእስራኤል አቻው ጋር የተፈራረመው ስምምነት የተገለፀ ሲሆን ከእስራኤል በቀረበ ግብዣ ወደ ስፍራው ማቅናታቸውና በ17 ዓመት ቡድኖች መካከል ሁለት የወዳጅነት ጨዋታዎች ከመደረጋቸው ባሻገር በሰባት ነጥቦች ላይ የመግባቢያ ስምምነት መፈራረማቸው ተገልጿል።

በአሰልጣኞች ትምኅርት፣ በአዋቂዎች እና ወጣቶች እግርኳስ እድገት፣ በወዳጅነት ጨዋታ፣ በእግርኳስ ልማት፣ በአስተዳደር ክህሎት እና እውቀት ሽግግር፣ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ እና ዲጂታላይዜሽን እንዲሁም በአስተዳደር እና ፋይናንስ እገዛ ላይ ያተኮረ የመግባቢያ ሰነድ የተፈራረሙ ሲሆን አቶ ባሕሩ በተጨማሪ እንደገለፁት ደግሞ ለኢትዮጵያ የመጫወት ፍላጎት ያላቸው ትውልደ ኢትዮጵያውያንን አግኝተን ውይይት ለማድረግ መሞከራቸውን እና ስንታየሁ ሳላሊች የመጫወት ፍላጎቱን መግለፁን ጠቁመዋል። “ከፊፋ ስፖርት ፓስፖርት ጋር ተያይዞ ህጉ ምን ይላል የሚለውን አገናዝበን፤ ጠንካራ ብሔራዊ ቡድን እንዲኖረን ከመፈለግም አንፃር ሌሎች ፍላጎት ያላቸውን ተጫዋቾች እየፈለግን ለብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ መረጃ የምንሰጥ ይሆናል።” ሲሉም አክለዋል።

አቶ ባህሩ ከስምምነቱ በተጎዳኝ በመሠረተ ልማት ጉዳዮች ላይ ተሞክሮ መውሰዳቸውን ተናግረል። ” በእስራኤል በነበረን ቆይታ ከመሠረተ ልማት ጋር ተያይዞ የተጫወትንበት ሜዳ ትንሽ ቢሆንም የፊፋ ስታዳርድን በሚገባ የጠበቀ ነው። እኛስ ስታዲየሞቻችንን በምን መልኩ ነው መስራት ያለብን የሚለውን ትልቅ ተሞክሮ ወስደን የመጣንበት ነበር። ” ብለዋል።

ከእስራኤሉ ጉዞ ጋር በተያያዘ ከጋዜጠኞች ከቀረቡት ጥያቄዎች መካከል አንድ ግብ ጠባቂ ብቻ እና ያለ ግብ ጠባቂ አሰልጣኝ ስለመጓዛቸው ተጠይቆ ግብ ጠባቂውን እና አሰልጣኙን ስም የእስራኤል ኤምባሲ ባለማሳለፉ መሆኑ ተገልጿል።

መግለጫው ከተጠራበት ዋነኛ አጀንዳ በተጨማሪ ከፊታችን ቅዳሜ ጀምሮ በኢትዮጵያ የሚስተናገደው የሴካፋ ውድድር መራዘሙ ተገልጿል። ከካፍ የሚለቀቀው በጀት ጁላይ መጀመርያ ላይ የሚለቀቅ በመሆኑ እና አንዳንድ ሀገራት በፊፋ አረብ ዋንጫ ላይ እየተሳተፉ በመሆኑ የሴካፋ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ባደረገው ስብሰባ ከሰኔ 26 እስከ ሐምሌ 12 ድረስ እንዲደረግ ቀነ ቀጠሮ ተይዞለት የነበረው ይህ ውድድር የሚጀመርበት ቀን በሁለት ሳምንት እንዲገፋ ተደርጎ ከሐምሌ 10 (ጁላይ 17) ጀምሮ እንዲደረግ መወሰኑ ተጠቁሟል።

ፕሬዝዳንት ኢሳይያስ የውድድሩ መራዘም ከዝግጅቱ ጋር የተያያዘ እንዳልሆነ ጠቁመዋል። ” ልትረዱ የሚገባው ኢትዮጵያ እንዲራዘም አልጠየቀችም። እኛ በብዙ ረገድ ዝግጁ ነበርን። የሴካፋ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ባደረገው ስብሰባ የየሀገራቱን ችግር ከሰበሰበ በኋላ የወሰነው ውሳኔ ነው። ብሔራዊ ቡድናችን ለረጅም ጊዜ ልምምድ ላይ መቆየቱ ጉዳት እንዳለው ይታወቃል። ነገር ግን የአብዛኛዎቹም ተመሳሳይ ነው። ካፍ የሚለቀው ገንዘብ ለውድድሩ ያስፈልገናል። ከጁላይ ጀምሮ ስለሚለቁት ነው ውድድሩም ወደ ጁላይ 17 የተዛወረው። ” ሲሉ ፕሬዝዳንቱ ተናግረዋል።

ዋና ፀሐፊው አቶ ባሕሩም የፕሬዝዳንቱን ሀሳብ በመጋራት ” እኛ ባልጠበቅነው ሁኔታ ነው የተራዘመው። ለማዘጋጀት ዝግጁ ነበርን። የአዘጋጅ ኮሚቴውን እንቅስቃሴም ከአንድም ሁለት ጊዜ ባህር ዳር በመገኘት በመገምገም እየሰራን እንገኝ ነበር። ውድድር ለማድረግ የሚያስፈልጉ ሥራዎችን ለመሥራት ወጪዎች ቢኖሩም አሳማኝ በሆነ ምክንያት በመራዘሙ ብዙም ቅሬታ ማቅረብ አንፈልግም። ” ብለዋል።