ሪፖርት | ወልቂጤ ከተማ ጣፋጭ ድል ተቀዳጅቷል

ወልቂጤ ከተማ እና ሀምበሪቾ ዱራሜን ያገናኘው የሁለተኛ ሳምንት የመጨረሻ መርሐ-ግብር ወልቂጤ ከተማን ባለ ድል አድርጎ ተፈፅሟል።

በአሠልጣኝ ጻውሎስ ጌታቸው የሚመራው ወልቂጤ ከተማ በመጀመሪያው ጨዋታ ከጅማ አባጅፋር ጋር ተጫውቶ ነጥብ ከተጋራበት ቋሚ ስብስብ አህመድ ሁሴንን ብቻ በበሀይሉ ተሻገር ለውጦ ጨዋታውን ቀርቧል። እንደ ወልቂጤ ሁሉ በመጀመሪያው ጨዋታ ሦስት ነጥብ ያላገኘው (በሽንፈት) ሀምበሪቾ ሽንፈት ካስተናገደበት ጨዋታ ሦስት ለውጦችን አድርገዋል። አሠልጣኝ ግርማ ታደሠ በለውጦቹም ርሆቦት ሶለሎ፣ በረከት ወንድሙ እና ብሩክ ኤልያስን አሳርፈው አምረላ ደልታታ፣ ሙሉነህ ገ/መድን እና አላዛር አድማሱን አሰላለፍ ውስጥ አካተዋል።

የጨዋታውን የሀይል ሚዛን ወደ ራሳቸው አድርገው መጫወት የጀመሩት ወልቂጤዎች ቶሎ ቶሎ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ለመድረስ ሲጥሩ ታይቷል። በዚህም ጨዋታው በተጀመረ በ8ኛው ደቂቃ ይበልጣል ሽባባው በተከላካዮች መሐል ሮጦ ባገኘው ኳስ ነገር ግን እጅግ በወረደ አጨራረስ ሳይጠቀምበት ባመከነው አጋጣሚ መሪ ሊሆኑ ነበር። ከአምስት ደቂቃዎች በኋላም ቡድኑ የቆመን ኳስ መነሻ ባደረገ ዕድል ሌላ የግብ ማግባት ሙከራ አድርጎ መክኖበታል።

ሀምበሪቾዎች በበኩላቸው በአብዛኛው የመስመር ላይ አጨዋወታቸውን በማዘውተር ፈጣን ሽግግሮችን በሁለቱ መስመሮች በኩል ሲያደርጉ ታይቷል። በተለይም መስቀሉ ለቴቦ እና አልዓዛር አድማሱ ወደ ፊት እየሄዱ የሚፈጥሩት የግብ ማግባት አጋጣሚ ለወልቂጤዎች ፈተና ነበር። በዚህ አጨዋወትም በ19ኛው ደቂቃ በዳግም በቀለ አማካኝነት ጥሩ የግብ ማግባት አጋጣሚ ፈጥረው ነበር።

ጨዋታው ቀጥሎ 35ኛው ደቂቃ ላይ ሲደርስ መሪ አግኝቷል። በተጠቀሰው ደቂቃ ላይ ራሱን ነፃ አድርጎ በተጋጣሚ የፍፁም ቅጣት ምት ክልል ውስጥ የተገኘው ረመዳን የሱፍ ከቀኝ መስመር የተሻገረለትን ኳስ በቅድሚያ ሲሞክር ግብ ጠባቂው እሸቱ አጪሶ ይመልስበታል። ራሱ ረመዳን የግብ ዘቡ የመለሰውን ኳስ ዳግም አግኝቶ ከመረብ ጋር በማዋሀድ ወልቂጤ ከተማ መሪ ሆኗል። ግቡ ከተቆጠረ ከአምስት ደቂቃዎች በኋላም እጅግ በጥሩ ሁኔታ ተጋጣሚያቸውን ሲያስጨንቁ የነበሩት ወልቂጤዎች ሁለተኛ ጎል አስቆጥረዋል። በዚህ ደቂቃም አቡበከር ሳኒ በተከላካዮች መሐል የደረሰውን ኳስ በጥሩ እርጋታ የግብ ጠባቂው ጀርባ የሚገኘው መረብ ላይ አሳርፎታል።

ጨዋታው ከቁጥጥራቸው ውጪ እየሆነ የመጣው ሀምበሪቾዎች የመጀመሪያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ ሦስት ደቂቃ ሲቀረው ከመዓዘን ምት የተነሳን ኳስ በመጠቀም በጨዋታው ያላቸውን ተስፋ ለማለምለም ሞክረዋል። ነገርግን ተከላካዩ አቤኔዘር ኦቴ በግንባሩ የሞከረው ኳስ ዒላማው ስቶ የግቡን አግዳሚ ታኮ ወደ ውጪ ወጥቷል። የመጀመሪያው የጨዋታ ክፍለ ጊዜም በወልቂጤ ከተማ 2-0 መሪነት ተገባዷል።

የሁለተኛው አጋማሽ እንደተጀመረ ወደ ጨዋታው የሚመልሳቸውን ጎል ለማግኘት ሲጣጣሩ የነበሩት ሀምበሪቾዎች በ49ኛው ደቂቃ ነጋሽ ታደሠ ሳጥኑ ጫፍ ሆኖ በሞከረው ጥቃት የወልቂጤን መረብ ፈትሸዋል። ነገርግን ተጫዋቹ የሞከረው ኳስ ዒላማውን ስቶ ወደ ውጪ ወጥቷል። ከዚህ ሙከራ በተጨማሪም ቡድኑ ረጃጅም ኳሶችን በማዘውተር ለመጫወት ጥሯል። በተለይም የቅጣት ምት እና የመዓዘን ምትን እንደ ዋነኛ የግብ ማግኛ መንገድ በመከተል ሲጫወቱ ታይቷል።

የቤት ሥራቸውን በመጀመሪያው አጋማሽ የጨረሱ የሚመስለው ወልቂጤ ከተማዎች ደግሞ ጥቃት መሰንዘራቸውን ጋብ አድርገው ኳስን ማንሸራሸር እና የሀምበሪቾ ተጫዋቾች ክፍተቶችን እንዳያገኙ መልፋት ተያይዘዋል። ጨዋታው 71ኛው ደቂቃ ላይ ሲደርስ ደግሞ የአሠልጣኝ ጻውሎስ ጌታቸው የተጫዋች ለውጥ ፍሬ አፍርቶ ቡድኑ ሦስተኛ ጎል አስቆጥሯል። በዚህም በ69ኛው ደቂቃ ፍሬው ሠለሞንን ለውጦ ወደ ሜዳ የገባው አህመድ ሁሴን አብዱልከሪም ወርቁ ላይ የተሰራውን ጥፋት ተከትሎ የተገኘውን የቅጣት ምት ረመዳን ሲያሻማው በግንባሩ አግኝቶ ጎል አስቆጥሯል።

ሙሉ የጨዋታው ክፍለጊዜው ሊገባደድ አምስት ደቂቃዎች ሲቀሩት ወልቂጤዎች የግብ ልዩነቱን ወደ አራት ከፍ ለማድረግ ጥረዋል። በቅድሚያም በሀይሉ ተሻገር ከሳጥኑ ጫፍ ሆኖ ጥሩ ጥቃት ቢፈፅምም የግብ ዘቡ እሸቱ አጪሶ አውጥቶበታል። በመቀጠል ደግሞ ከመዓዘን የተሻገረው ኳስ ሲመለስ ከሳጥን ውጪ የነበረው ዮናስ በርታ አክርሮ መትቶት የነበረ ቢሆንም ኳስ ለጥቂት ወደ ውጪ በመውጣቷ ግብ ሳይቆጠር ቀርቷል። የዕለቱ አራተኛ ዳኛ ጭማሪ ደቂቃ ለማሳየት በሚዘጋጁበት ወቅት ደግሞ አህመድ ሁሴን ከተከላካዮች ጀርባ በመሮጥ ያገኘውን ኳስ በማስቆጠር የማሳረጊያው ጎል ተስተናግዷል። በጨዋታው ከፍተኛ ብልጫ የተወሰደባቸው ሀምበሪቾዎች እጃቸውን ለወልቂጤ ሰጥተው ጨዋታው 4-0 ተጠናቋል።

ውጤቱን ተከትሎ ሦስት ነጥብ ያገኙት ወልቂጤ ከተማዎች ነጥባቸውን አራት በማድረስ የሁለተኛ ደረጃን ይዘዋል። ከሁለቱም ጨዋታዎች አንድም ነጥብ ያላገኘው ሀምበሪቾ ዱራሜ ደግሞ በደረጃ ሠንጠረዡ ግርጌ ላይ ተቀምጧል።