በስፖርት ጋዜጠኝነት ከ25 ዓመታት በላይ ያገለገለው ጋዜጠኛ ሊመሰገን ነው

በኢትዮጵያ ስፖርት ላይ ለሩብ ምዕተ ዓመት ለሰራው ጋዜጠኛ መሸሻ ወልዴ የምስጋና እና የእውቅና አሠጣጥ ዝግጅት ሊከናወን ነው።

በሁሉም የስፖርት አይነቶች፣ በሁለቱም ፆታዎች እና በሁሉም የዕድሜ እርከን ውድድሮች ላይ በመገኘት በሻምፒዮን፣ ማራቶን፣ ግሎባል፣ ይድነቃቸው፣ ካታናንጋ፣ አዲስ ስፖርት፣ ካምቦሎጆ፣ ሊግ ስፖርት፣ ሀትሪክ ስፖርት (መፅሔትም) ጋዜጦች እና በቤስት ስፖርት መፅሔት እንዲሁም በኤፍ ኤም 90.7 (ዛሚ) እና 96.3 ለስፖርት ቤተሰቡ የተለያዩ መረጃዎችን ላለፉት 25 ዓመታት ሲያደርስ የቆየው (አሁንም እያደረሰ የሚገኘው) ጋዜጠኛ መሸሻ ወልዴ ለሰራው ስራ ለማመስገን እና ለልፋቱ እውቅና ለመሰጠት በግል ተነሳሽነት በተዋቀረ ኮሚቴ ስራዎች መከወን ጀምረዋል። 8 አባላት ያሉት ኮሚቴ ከ20 ቀናት በፊት ጀምሮ ለምስጋና እና እውቅና ዝግጅቱ ስራዎችን ሲሰራ የቆየ ሲሆን ከትናንት በስትያ ደግሞ የዝግጅቱን ሙሉ ሂደት የተመለከተ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።

“መሸሻን እናመሠግናለን” በሚል መሪ ቃል ለሚቀጥሉት ሁለት ወራት የሚቆየው ዝግጅት በሦስት ክፍሎች ተከፋፍሎ እንደሚደረግ ሲገለፅ በመጀመሪያው ክፍል ስለ መሸሻ ወልዴ እውቅና አሠጣጥ የማስተዋወቅ ሥራ ይከናወናል። በሁለተኝነት ደግሞ እውቅና ለመስጠት የሚያስፈልገውን ገንዘብ የማሰባሰብ ሥራ እንደሚደረግ ሲብራራ በመጨረሻው ክፍል የእውቅና አሠጣጡ እንደሚከናወን ተገልጿል። በተለያዩ አማራጮች የእውቅና አሠጣጡ እንዲተዋወቅ ከተደረገ በኋላ ከተለያዩ አካላት (በውጪ ሀገር የሚገኙ የስፖርት ቤተሰቦችን ጨምሮ) በራሱ መሸሻ ወልዴ ስም የተከፈቱት ዝግ አካውንቶች ላይ ገንዘብ እንዲሰባሰብ ይደረጋል ተብሏል።

የገንዘብ አሰባሰቡ ሂደት እየተከናወነ መሸሻ የሰራውን ስራ የተመለከተ እና አጠቃላይ የህይወት ታሪኩን እንዲሁም በስፖርት ያሳለፋቸውን ዓመታት የሚያሳይ ዘጋቢ ፊልም እንደሚዘጋጅ ተጠቁሟል። በሰባት ባንኮች የሚሰበሰበው የገንዘብ መጠን ከታወቀ በኋላ ደግሞ ለመሸሻ ወልዴ ስጦታ የሚሆን ነገር ለማዘጋጀት እንደታሰበ ለዚህ ዝግጅት የተቋቋመው ኮሚቴ አባል አቶ ሠለሞን ተሾመ ነግረውናል። በዋናነት ደግሞ ጋዜጠኛው ዘለቄታዊ ጥቅም ያለው ነገር እና ቤተሰቡን ሊደግፍ የሚችል ሥራ የማመቻቸት ተግባር ይከናወናል ተብሏል።

በጎ ዓላማ ያለው የእውቅና አሠጣጥ ስራው ከሰኔ ወር ሁለተኛ ሳምንት ጀምሮ እስከ ነሐሴ ወር መጨረሻ ሳምንት ድረስ እንደሚዘልቅ ያስረዱን አቶ ሠለሞን የመዝጊያ መርሐ-ግብሩ ጿጉሜ 4 ጥሪ የሚደረግላቸው እንግዶች በተገኙበት በደማቅ ሁኔታ መቋጫውን እንደሚያገኝ አመላክተዋል።

ለዚህ የእውቅና አሠጣጥ ዝግጅት ማስፈፀሚያ በመሸሻ ወልዴ ስም (በዝግ) የተከፈቱት የሂሳብ ቁጥሮች የሚከተሉት ናቸው:-

ዩናይትድ ባንክ : (1140411652300018)
አዋሽ ባንክ : (01320499727900/8350)
ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ : (1000414344732)
ኦሮሚያ ባንክ : (1000800011845)
ወጋገን ባንክ : (0886934530101)
አቢሲኒያ ባንክ : (57534378)
ዳሽን ባንክ : (5026018283)