የፕሪምየር ሊግ ክለቦች የማሟያ ጨዋታዎች የነገ ውሎ

ነገ የሚደረጉት የሦስተኛ ሳምንት የፕሪምየር ሊግ ክለቦች የማሟያ ሦስት ጨዋታዎችን እንደሚከተለው ዳሰናቸዋል።

የትግራይ ክልል ክለቦች በ2014 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የማይሳተፉ ከሆነ በምትካቸው የሚወዳደሩትን ክለቦች ለመለየት የሚደረገው ውድድር ወደ ወሳኝ ምዕራፍ እየተሸጋገረ ይገኛል። በሀዋሳ ዩኒቨርስቲ ስታዲየም እየተደረገ የሚገኘው ፍልሚያም ነገ በሦስት ጨዋታዎች ቀጥሎ ይደረጋል።

👉ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከ ኮልፌ ቀራኒዮ ክ/ከ (3:30)

የውድድሩን የመጀመሪያ ሦስት ነጥብ ጅማ አባጅፋር ላይ ያሳካው ኢትዮ ኤሌክትሪክ ድል ባደረገበት ጨዋታ ያሳየው ብቃት መልካም የሚባል ነበር። እርግጥ ቡድኑ በአዳማም ሲረታ ጥሩ እንደነበረ ቢታይም በጅማው ጨዋታ ግን ጫናዎችን የተቆጣጠረበት እና የግብ ማግባት አጋጣሚዎችን ለመፍጠር ሲሄድበት የነበረው መንገድ ጥሩ ነበር። በተለይ የቡድኑ የመስመር አጥቂዎች አደም አባስ እና ኤርሚያስ ኃይሉ የሜዳውን ስፋት በፍጥነታቸው ለመጠቀም ሲያደርጉ የነበረው ጥረት ነገም የሚደገም ከሆነ ለኮልፌ ፈተና እንደሚሆን ይታሰባል። ይህ በእንዲህ እንዳለ በጅማው ጨዋታ በተሻጋሪ ኳሶች እጅግ ሲፈተን የነበረው የአሠልጣኝ ክፍሌ ቡድን ነገ ይሄንን ክፍተቱን ጠግኖ ካልገባ አደጋ ላይ ሊወድቅ ይችላል።

ከብዙ ገለልተኛ ተመልካቾች ተወዳጅነት ያገኘው ኮልፌ ከኳስ ጋር የሚያሳልፈው ጊዜ እጅግ ማራኪ ሆኖ ይታያል። በተለይ በመጀመሪያው የሀምበሪቾ ጨዋታ ላይ የነበረው የቡድኑ ፍሰት ያለው ቀጥተኛ አጨዋወት አስገራሚ ነበር። በሁለተኛ ሳምንት የውድድሩ ጨዋታ የቀረበው የአሠልጣኝ መሐመድኑር ንማ ቡድን ግን ብዙ ጥያቄዎች ነበሩበት። እርግጥ አሠልጣኙ አራት ለምንም ከተጠናቀቀው ጨዋታ በኋላ “ተጫዋቾቼ በወኪሎች እንዲረበሹ ተደርጓል” የሚል ሀሳብ ለሶከር ኢትዮጵያ ሰጥተው የሽንፈቱን ምክንያት ቢያስቀምጡም በሜዳ ላይ በአራቱም የሜዳ ክፍሎች የታየው የተጫዋቾች የትኩረት ማነስ እና ዝንጉነት ችግር በጉልህ ቡድኑን ዋጋ እንዳስከፈለው ተስተውሏል። ይህ ክፍተት ነገ ታርሞ ከመጣ እና ቡድኑ እንደ መጀመሪያው ጨዋታ ፍጥነት ያላቸው ቅብብሎችን በማድረግ ቶሎ ቶሎ ወደ ተጋጣሚ ሳጥን የሚደርስ ከሆነ ኤሌክትሪክ ሊፈተን ይችላል።

👉ጅማ አባጅፋር ከ ሀምበሪቾ ዱራሜ (7:00)

በሁለት ጨዋታዎች ሦስት ነጥብ ያላገኙት ጅማ እና ሀምበሪቾ ነገ እርስ በእርስ የሚያደርጉት ፍልሚያ ጥሩ ፉክክር እንደሚደረግበት ይታመናል። በአሠልጣኝ ፀጋዬ የሚመራው ጅማ ደግሞ በወልቂጤውም ሆነ በኤሌክትሪኩ ጨዋታ እንደተጫወተው የአየር ላይ ጥቃቶችን ለመሰንዘር እንደሚሞክር ይገመታል። በተለይ ቁመታሙን የመሐል አጥቂ ራሂም ኦስማኖን ዒላማ ያደረጉ ተሻጋሪ እና ረጃጅም ኳሶችን በማብዛት የሀምበሪቾን ጊዜ ከባድ ሊያደርግ ይችላል። ከዚህ ውጪ የሁለቱ የመስመር አጥቂዎች (ተመስገን እና ፕሪንስ) ፍጥነት ለቡድኑ ሌላ ግብ የማስቆጠሪያ አማራጭ ሊሆን እንደሚችል እሙን ነው። ይህ ቢሆንም ግን የተጠቀሱት አጥቂዎች የስልነት ችግር ቡድኑን እጅግ አስፈላጊውን ጨዋታ ለራሱ በጎ ነገር እንዳያመጣበት እንዳያደርገው ያሰጋል።

እስካሁን ብቸኛው አንድም ነጥብ በውድድሩ ያላገኘው ክለብ ሀምበሪቾ ዱራሜ ነው። በመጀመሪያው ጨዋታ ለኮልፌ በሁለተኛው ጨዋታ ደግሞ ለወልቂጤ ከተማ ሦስት ነጥብ ያስረከበው ቡድኑ ወሳኝ ተጫዋቾቹን አጥቶ የሚያደርጋቸው ጨዋታዎች እጅግ የፈተኑት ይመስላል። በተለይ በወልቂጤው ጨዋታ የቡድኑ የመከላከል አደረጃጀት ክፍተቶች የነበሩበት ነበሩ። ከምንም በላይ ቡድኑ ከማጥቃት ወደ መከላከል የሚደርገው ሽግግር ጊዜው የሰፋ እና ለተጋጣሚ ክፍተቶችን የሚተው ነበር። ይህ ለአደጋ የቀረበ የመከላከል አደረጃጀት ነገም ካልተቀረፈ ቡድኑ ወደ ፕሪምየር ሊግ ለመግባት ያገኘውን የመጨረሻ ዕድል አጥቦ ይወጣል። የአሠልጣኝ ግርማ ታደሠ ቡድኑ ከላይ የተጠቀሰው ክፍተት ቢኖርበትም የመስመር ተከላካዮቹ መስቀሉ ለቴቦ እና አልዓዛር አድማሱ ያላቸው የማጥቃት ፍላጎት ጥሩ ነው። ሁለቱም በተደጋጋሚ ወደ ፊት እየሄዱ ለዳግም በቀለ የሚያሻግሯቸው ኳሶችም ነገ ዒላማቸውን የሚጠብቁ ከሆነ ምናልባት ሀምበሪቾ ከድል ጋር ሊታረቅ የሚችልበት አጋጣሚ ሊፈጠር ይችላል።

👉ወልቂጤ ከተማ ከ አዳማ ከተማ (10:00)

በደረጃ ሠንጠረዡ አናት ላይ ሆነው የሚገናኙት ወልቂጤ ከተማ እና አዳማ ከተማ የሚያደርጉት የሦስተኛ ሳምንት ሦስተኛ መርሐ-ግብር ትልቅ ግምት አግኝቷል። አራት ግቦችን ተጋጣሚያቸው ላይ አስቆጥረው ነገ የሚገናኙት ወልቂጤ እና አዳማ በፕሪምየር ሊጉ መተዋወቃቸው እና የተሻሉ ተጫዋቾች መያዛቸው ጨዋታው በጉጉት እንዲጠበቅ አድርጎታል።

የአሠልጣኝ ጻውሎስ ጌታቸው ቡድን ወልቂጤ ከዚህ በፊት የነበረበትን የግብ ፊት አይናፋርነት ችግር በሀምበሪቾው ጨዋታ የቀረፈ ይመስላል። በተለይ በሦስተኛው የሜዳ ክፍል ላይ የመረጋጋት እና የውሳኔ አሰጣጥ ችግር የነበረበት ቡድኑ ከወገብ በላይ ስል ሆኖ ታይቷል። ይህ በጎ ጎን ነገም የሚደገም ከሆነ ወልቂጤ ሊያተርፍ ይችላል። ከምንም በላይ አሠልጣኙ እንደ ሀምበሪቾው ጨዋታ በርካታ የማጥቃት ባህሪ ያላቸው ተጫዋቾችን ወደ ሜዳ የሚያስገቡ ከሆነ የአዳማ ተከላካዮች ትልቅ የራስ ምታት የሚመጣባቸው ይሆናል። አዎንታዊው ነገር እንደተጠበቀ ሆኖ ወደ መሐል ሜዳ እጅግ ተጠግቶ በጀብደኝነት የሚጫወተው የኋላ መስመሩ በፈጣኖቹ የአዳማ አጥቂዎች እንዳይቸገር ያሰጋል።

ማግኘት የሚገባውን ስድስት ነጥብ ያሳካው እና የትግራይ ክልል ክለቦች በሊጉ ካልተሳተፉ በሊጉ መቆየቱን ለማረጋገጥ ከጫፍ የደረሰ የሚመስለው አዳማ ከተማ ከቀሪ ሦስት ጨዋታዎች አራት ነጥብ የሚያሳካ ከሆነ ውጥኑን ከዳር ያደርሳል። በኮልፌው ጨዋታ በብዙ መስፈርቶች ተሻሽሎ የቀረበው አዳማ የኮልፌን የኳስ ፍሰት አጨዋወት በላይኛ ሜዳ ፈቅዶ ወደ ራሱ ሜዳ ሲመጡ የተከተለው ጥብቅ ተጭኖ የመጫወት ስልት አዋጥቶት ነበር። በራሱ ሜዳ በቁጥር በዝቶ የተቀበለውን ኳስ ደግሞ በፍጥነት ወደ ፊት በማድረስ ተጋጣሚ ሳይደራጅ ለጥቃት የሚያመቻችበት መንገድ ፍሬያማ አድርጎት ግቦችን አስቆጥሯል። ነገም ወልቂጤ ይኖረዋል ተብሎ ከሚጠበቀው የኳስ ቁጥጥር የበላይነት መነሻነት ቡድኑ ተመሳሳይ የጨዋታ መንገድ ቀይሶ ወደ ሜዳ ሊገባ ይችላል። ከዚህ ውጪ የቡድኑ የቆሙ ኳሶች አጠቃቀም ለወልቂጤ ሌላቸው ፈተና እንደሚሆን ይታመናል።