ሪፖርት | አዳማ ከተማ በማሟያ ውድድር የመጀመሪያው አላፊ ሆኗል

የትግራይ ክልል ክለቦች በሊጉ ካልተሳተፉ ሀምበሪቾን 2-1 ያሸነፈው አዳማ ከተማ እነርሱን ከሚተኩት መካከል የመጀመሪያው ክለብ መሆኑን አረጋግጧል።

ከድል ጋር ለመታረቅ ወደ ሜዳ የገቡት ሀምበሪቾዎች በጅማ አባጅፋር ከተረቱበት ጨዋታ ሦስት ለውጦችን አድርገዋል። በዚህም አሠልጣኝ ግርማ ታደሠ ፀጋአብ ዮሴፍ፣ ነጋሽ ታደሰ እና ብሩክ ኤልያስ አሳርፈው አምረላ ደልታታ፣ ቢኒያም ጌታቸው እና ተመስገን አሠፋን ወደ ሜዳ አስገብተዋል። በተቃራኒው ከወልቂጤ ከተማ ጋር ጥሩ ፉክክር አድርገው አንድ ነጥብ የተጋሩት አዳማ ከተማዎች ደግሞ አንድ ለውጥ ብቻ አድርገው ወደ ሜዳ ገብተዋል። በዚህም የአጥቂ መስመር ተጫዋቹ በላይ ዓባይነህ አርፎ ኤሊያስ ማሞን ቋሚ ሆኗል።

ቀዝቀዝ ያለ እንቅስቃሴ ማስመልከተ የጀመረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ለግብ የቀረበ ሙከራ ለማስተናገድ 12 ደቂቃ ወስደውበት ነበር። በተጠቀሰው ደቂቃ ላይ ግን የመሐል አጥቂው አብዲሳ ጀማል የግል ጥረቱን ተጠቅሞ ወደ ሳጥን ሊገባ ሲል ጥፋት ተሰርቶበት አዳማ አደገኛ ቦታ ላይ የቅጣት ምት አግኝቷል። የተገኘውን የቅጣት ምትም የቡድኑ አምበል ኤልያስ ማሞ በድንቅ ሁኔታ እሸቱ አጪሶ መረብ ላይ አሳርፎት አዳማ ከተማ ጨዋታው ገና ሩብ ሰዓት ሳይሞላው መሪ ሆኗል። ግቡ ከተቆጠረ በኋላም የአዳማ ከተማ ተጫዋቾች ከሦስት ቀን በፊት የልጅ አባት የሆነው አሠልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ ጋር በመሄድ ደስታቸውን ልጅ የማቀፍ ምልቅት በማሳየት ገልፀዋል።

ብልጫ ወስደው መጫወት የቀጠሉት አዳማዎች ኳስን ከተጋጣሚያቸው በተሻለ በማንሸራሸር መጫወት ይዘዋል። በ25ኛው ደቂቃም ቡድኑ በአብዲሳ ጀማል አማካኝነት ጥሩ ጥቃት ፈፅሞ መሪነቱን ወደ ሁለት ከፍ ለማድረግ ጥሯል። በአመዛኙ ወደ ራሳቸው የሜዳ ክልል አፈግፍገው መጫወትን ምርጫቸው ያደረጉት ሀምበሪቾዎች ጠጣሩን የአዳማ የኋላ መስመር ማለፍ ተስኗቸው ጨዋታው ቀጥሏል። ይባስ ብሎ በ38ኛው ደቂቃ ላይ ተጨማሪ ጎል አስተናግደው ራሳቸውን አጣብቂኝ ውስጥ ከተዋል። በተጠቀሰው ደቂቃ ላይ በቃሉ ገነነ እና ኤልያስ ማሞ አንድ ሁለት ተቀባብለው የመጨረሻው ኳስ የደረሰው በቃሉ የግል ጥረቱን ተጠቅሞ ተጫዋቾችን ካለፈ በኋላ ከሳጥን ውጪ ሆኖ እጅግ ድንቅ ጎል አስቆጥሯል። በቀሪዎቹ የአጋማሹ ደቂቃዎች ሁለቱም ቡድኖች ምንም የጠራ የግብ ማግባት ሙከራ ሳያደርጉ የመጀመሪያው አጋማሽ በአዳማ መሪነት ተጠናቋል።

ወደ ጨዋታው ለመመለስ እጅግ ከፍተኛ መታተር የሚጠበቅባቸው ሀምበሪቾዎች የሁለተኛው አጋማሽ እንደተጀመረ ሁለት ጥቃቶችን ከሳጥን ውጪ ቢሞክሩም ውጥናቸው ሳይሰምር ቀርቷል። አሠልጣኝ ግርማ ታደሠም አጋማሹ በተጀመረ በአምስት ደቂቃዎች ውስጥ ሦስት የማጥቃት ባህሪ ያላቸው ተጫዋቾችን በማስገባት ጨዋታው ላይ ያላቸውን ቆይታ ለማርዘም ጥረዋል። አዳማዎች በበኩላቸው በመጀመሪያው አጋማሽ ሲሰነዝሩት የነበረውን ጫና ጋብ አድርገው በእጃቸው የገባውን ሦስት ነጥብ አሳልፎ ላለመስጠት መልፋት ይዘዋል።

ጨዋታው 70ኛው ደቂቃ ላይ ሲደርስ ሀምበሪቾዎች የመጀመሪያውን ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ አድርገዋል። በዚህ ደቂቃም የአዳማ ተጫዋቾች የሰሩትን የቅብብል ስህተት ያገኘው አምረላ ደልታታ ለዋቁማ ዲንሳ ጥሩ ኳስ አመቻችቶለት ዋቁማ ጥሩ ጥቃት ሰንዘሯል። ከስምንት ደቂቃዎች በኋላ ደግሞ ቡድኑ ኳስ እና መረብን አገናኝቶ በጨዋታው ላይ ያለውን ተስፋ አለምልሟል። በተጠቀሰው ደቂቃ አቤኔዘር ኦቴ ወደ ግራ ባዘነበለ ቦታ ላይ ያገኘውን ኳስ በጥሩ አጨራረስ መረብ ላይ አሳርፎታል።

በቀሪዎቹ ደቂቃዎች ሀምበሪቾዎች በተለይ በሁለቱ መስመሮች ላይ ያተኮረ ጥቃት በመሰንዘር ቢያንስ አንድ ነጥብ ለማግኘት ቢጥሩም በመጀመሪያው አጋማሽ ከመስቀሉ ለቴቦ ጋር ተጋጭቶ ጥርሱ ላይ አደጋ ያጋጠመው ሚሊዮን ሠለሞን እና ጀሚል ያቆብ ቦታቸውን በሚገባ በማስከበር ቡድናቸው ሦስት ነጥብ ይዞ እንዲወጣ ረድተዋል። ጨዋታውም ተጨማሪ ጎል ሳያስተናግድ በአዳማ ከተማ አሸናፊነት ተጠናቋል።

ውጤቱን ተከትሎ ነጥቡን አስር ያደረሰው አዳማ ከተማ የትግራይ ክልል ክለቦች በሊጉ የማይሳተፉ ከሆነ አንዱን ቦታ እንደሚይዝ አረጋግጦ ከሜዳ ወጥቷል። ሀምበሪቾዎች ደግሞ ወደ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ለማደግ የነበራቸውን ዕድል ሙሉ ለሙሉ አምክነው ያለ ምንም ነጥብ የደረጃ ሰንጠረዡ ግርጌ ላይ ተቀምጠዋል።