የአሠልጣኞች አስተያየት | ሀምበሪቾ 1-2 አዳማ ከተማ

(የትግራይ ክለቦች በቀነ ገደቡ ካልተመዘገቡ) አዳማ ከተማ ለከርሞ በፕሪምየር ሊጉ መቆየቱን ካረጋገጠበት እንዲሁም ሀምበሪቾ ከተማ ወደ ሊጉ ለማደግ የነበረውን የመጨረሻ ዕድል ሙሉ ለሙሉ ካመከነበት ጨዋታ በኋላ አሠልጣኞች አስተያየት ሰጥተውናል።

ዘርዓይ ሙሉ – አዳማ ከተማ

በማሟያ ውድድሩ የመጀመሪያው አላፊ ቡድን ሆናችኋል። ምን ተሰማህ?

በዚህ እጅግ በጣም ተደስቻለው። ቡድኑ እኔ ወደምደልገው መንገድ የመጣው በዚህኛው ውድድር ነው። ከምንም በላይ ደግሞ ዋነኛ ዓላማችንን አሳክተናል። መጀመሪያም ለቡድኑ ቃል ገብቼ ነበር። ይሄንን ውድድር አሸንፌ ክለቡን በፕሪምየር ሊግ ለማቆየር አቅጄ ነበር። ይሄንንም በማሳካቴ ደስተኛ ነኝ። ዓላማችን እንዲሳካ ደግሞ የነበረን አንድነት እና ህብረት ተጠቃሽ ነው። ለዚህ ደግሞ ተጫዋቾቼን በጣም አመሠግናለሁ። ይሄ ውጤት እንዲመጣ የክለቡ ፕሬዝዳንት እና ሥራ አስኪያጅ የከፈሉት መስዋትነት ትልቅ ነው። በተለያየ መንገድ ቡድኑን ሲያበረታቱ ነበር። ልምምድ ሜዳ ድረስ እየመጡ ያበረታቱን ነበር። ለዚህም ምስጋና ይገባቸዋል። የአዳማ ደጋፊዎችም እየደወሉ ሲያበረታቱኝ ነበር። እነርሱንም ማመስገን እፈልጋለሁ።

ጨዋታው እንዴት ነበር?

ጨዋታው ሁለት መልክ ነበረው። በመጀመሪያው አጋማሽ እነርሱ ይዘውት በመጡት አሰላለፍ ነው የተጠቀምነው። የ3-5-2 አሰላለፋቸውን ተጠቅመን 2-0 መርተን እረፍት ወጥተናል። ከእረፍት በኋላ በተለይ ከ25 ደቂቃ በኋላ ግን ተጫዋቾቼ ላይ ድካም ይታይ ነበር። ይሄም የሆነው ተደራራቢ ጨዋታዎችን ተጫዋቾቹ ስለመጣባቸው ነው። የቀየርኳቸውም ተጫዋቾች እንደተጠበቁት አልነበሩም። በዚህ መሐል ጎል ገባብን። አንድ ጎል ቢገባብንም ግን ውጤቱን ይዘን ወጥተናል።

የማሟያ ውድድሩ የመጀመሪያው አላፊ ሆናችኋል። አንድ ጨዋታም ይቀራችኋል። ከእሁዱ ጨዋታ ምን ይጠበቅ?

እስካሁን አልተሸነፍንም። ጎልም የገባብን ዛሬ ገና ነው። እሁድም ይሄንን ይዘን ወጥተን ውጤት ለማምጣት እንሞክራለን። ውድድሩንም በአንደኝነት ለማጠናቀቅ እንጥራለን።

ግርማ ታደሠ – ሀምበሪቾ ዱራሜ

ስለ ጨዋታው?

ቡድኔ ላይ በየጨዋታው የማየው ለውጥ ጥሩ ነው። ከነ ችግራችንም ቢሆን ጥሩ ነበርን። በተለይ የመከላከል ችግራችን አሁንም አልተፈታም። ለዚህ ደግሞ በተለያዩ ምክንያቶች ያጣናቸው ተጫዋቾች ዋጋ አስከፍለውናል። ቡድኑ ውጤታማ ባይሆንም እንዳልኩት መሻሻሎች አሉን። በአጠቃላይ ከተጫዋቾቼ የምጠብቀው ነገር በጨዋታው አግኝቻለሁ። ወደ ጎልነት እየተቀየረ ያለውም ከተጫዋቾቼ አቅም በላይ የሚፈጠር ስህተት ነው።

በዛሬው ጨዋታ ቡድንህ ላይ ያየከው ለውጥ ምንድን ነው?

በጅማው ጨዋታ ላይ የተከላካይ ክፍሌ የተሻለ ነበር። ዛሬ ግን በተከላካይ ክፍሉ ላይ ስህተት ተፈጥሮ ሁለት ጎል ሊቆጠርብን ችሏል። ከዚህ ውጪ ግን መሐል ላይ ያለው ነገር ጥሩ ነበር። ከምንም በላይ ደግሞ ከማጥቃት ቀደ መከላከል እና ከመከላከል ወደ ማጥቃት የሚደረገው ሽግግር ጥሩ ነበር።