ሪፖርት | ወልቂጤ ከተማ በማሟያ ውድድሩ የማለፉን ተስፋ አለምልሟል

የአራተኛ ዙር የመጨረሻ መርሐ-ግብር የሆነው የወልቂጤ እና ኤሌክትሪክ ጨዋታ ወልቂጤን ባለ ድል ሲያደርግ ኤሌክትሪክን ደግሞ በማሟያ ውድድሩ የማያልፍ ክለብ አድርጎ ተጠናቋል።

በሦስተኛ ዙር የውድድሩ መርሐ-ግብር በኮልፌ ቀራኒዮ ክ/ከ ሁለት ለምንም ተረተው ለዛሬው ጨዋታ የቀረቡት ኢትዮ ኤሌክትሪኮች ለግማሽ ደርዘን የተጠጋ ለውጥ በማድረግ ወደ ሜዳ ገብተዋል። በለውጦቹም ከረጅም ጊዜ በኋላ ወደ የተመለሰው ጫላ ድሪባን ጨምሮ ቢንያም ታከለ፣ አዲስ ነጋሽ፣ አንዳርጋቸው ይላቅ እና አቅሌሲያ ግርማ ግብ ጠባቂው ዘሪሁን ታደለን፣ ብሩክ ጌታቸው፣ ቢኒያም ትዕዛዙ፣ አደም አባስ እና ኤርሚያስ ኃይሉን ተክተው ወደ ሜዳ ገብተዋል። ከሦስት ቀናት በፊት ከአዳማ ከተማ ጋር አንድ ነጥብ የተጋሩት ወልቂጤዎች ደግሞ ፍሬው ሠለሞንን ብቻ በአህመድ ሁሴን ተክተው ጨዋታውን ጀምረዋል።

ቀዝቀዝ ያለ አጀማመር ያሳየው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ኳሶችን ቶሎ ቶሎ በመነጣጠቅ መደረግ ጀምሯል። በአንፃራዊነት የተሻለ አቀራረብ የነበራቸው ወልቂጤ ከተማዎች ግን ከኤሌክትሪክ በተሻለ የግብ ማግባት ሙከራዎችን ለማድረግ የላይኛው የሜዳ ክልል ላይ ይገኙ ነበር። ጨዋታው 19ኛው ደቂቃ ላይ ሲደርስም የመጀመሪያውን ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ አስተናግዶ ግብ ተቆጥሯል። በተጠቀሰው ደቂቃ ላይ ወደ ቀኝ ባዘነበለ ቦታ የቅጣት ምት ያገኙት ወልቂጤዎች ኳሱን በሀብታሙ ሸዋለም አማካኝነት አሻምተውት ግብ አግኝተዋል። ሀብታሙ ያሻገረውን ኳስ አሜ መሐመድ ሞክሮት የግብ ዘቡ ቢኒያም ታከለ ሲመልሰው በጥሩ አቋቋም ላይ የነበረው አህመድ ሁሴን አግኝቶ ግብ አስቆጥሯል።

ግቡ ከተቆጠረ ከአራት ደቂቃዎች በኋላ ዳግም የቅጣት ምት ያገኙት ወልቂጤዎች በተመሳሳይ የቆመውን ኳስ በሀብታሙ አማካኝነት ወደ ግብነት ለመቀየር ቢጥሩም ግብ ጠባቂው ቢንያም በጥሩ ቅልጥፍና አምክኖባቸዋል። አሁንም ኤሌክትሪክን ማስጨነቅ የቀጠለው የአሠልጣኝ ጻውሎስ ጌታቸው ቡድን በ29ኛው ደቂቃ ሁለተኛ ጎል አግኝቷል። በዚህ ደቂቃም ፈጣኑ የመስመር ተጫዋች አቡበከር ሳኒ ከግራ መስመር የተሻገረውን የመሬት ለመሬት ኳስ በጥሩ ጊዜ አጠባበቅ በአስፈላጊው ቦታ በመገኘት ኳስ እና መረብን አገናኝቷል።

ወደ ጨዋታው ለመመለስ ወዲያው ጥቃት መሰንዘር የጀመሩት ኤሌክትሪኮች ሁለተኛውን ግብ ካስተናገዱ ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ በአቅሌሲያ ግርማ አማካኝነት ጥሩ ሙከራ አድርገው ነበር። ነገርግን አጥቂው የሞከረው ኳስ ዒላማውን ስቶ በግቡ አናት ወደ ውጪ ወጥቷል። ሁለት ጎል ያላረካቸው ወልቂጤዎች ግን የመጀመሪያው አጋማሽ ተጠናቆ በታየው ሁለት ጭማሪ ደቂቃ መሪነታቸውን ለማስፋት ዳድተው ነበር። በተለይ አሜ እና በሀይሉ ከሳጥን ውጪ የሞከሯቸው ኳሶች ግብ ለመሆን ተቃርበው የነበረ ቢሆንም ውጥናቸው ሳይሰምር አጋማሹ ተጠናቋል።

ያላቸውን የመጨረሻ ዕድል ለመጠቀም አራት ተጫዋች ቀይረው ሁለተኛውን አጋማሽ የጀመሩት ኢትዮ ኤሌክትሪኮች በተሻለ ለመንቀሳቀስ ቢሞክሩም እስከ 71ኛው ደቂቃ ድረስ አንድም ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ አላደረጉም። ወልቂጤዎች በበኩላቸው ነጥባቸውን እንዲሁም ደረጃቸውን ያሳደጉበትን ሦስት ነጥብ ላለማጣት በአንፃራዊነት ለመከላከል ቅድሚያ ሰጥተው መጫወት ይዘዋል። እንደተገለፀው ኤልፓዎች ግን በ71ኛው ደቂቃ የቆመን ኳስ መነሻ ባደረገ አጋጣሚ ጀማል ጣሰውን ፈትነው ነበር።

ግብ ለማስቆጠር ነቅለው የወጡትን የኤሌክትሪክ ተጫዋቾች ሜዳ በፈጣን ሽግግር ለማጥቃት ያሰቡት ወልቂጤዎች በ66ኛው ደቂቃ የመጀመሪያውን ግብ ያስቆጠረው አህመድ ሁለተኛውን ግብ ላስቆጠረው አቡበከር አቀብሎት ሦስተኛ ጎል ለማግኘት ጥረዋል። ከአስር ደቂቃዎች በኋላ ደግሞ ኤርሚያስ ኃልሉ ላይ የተሰራን ጥፋት ተከትሎ የተገኘን የቅጣት ምት ኢትዮ ኤሌክትሪኮች በመጠቀም ግብ ለማግኘት ጥረዋል። በዚህም ተቀይሮ የገባው ሚካኤል ለማ ያሻገረውን ኳስ አንዳርጋቸው ይላቅ በግንባሩ ገጭቶት ለጥቂት ወጥቷል።

በጨዋታው የመጨረሻ ደቂቃዎች ዳግም ብልጫቸውን መልሰው ያገኙት ወልቂጤዎች ከኳስ ጋር የሚያሳልፉትን ጊዜ በማርዘም መጫወት ቀጥለዋል። ሙሉ የጨዋታ ክፍለ ጊዜው ተጠናቆ በተጨመረው ደቂቃ መባቻ ላይ ደግሞ በሀይሉ ተሻገር የኤሌክትሪክ ተጫዋቾች የሰሩትን ጥፋት ተከትሎ ያገኘውን ኳስ ወደ ግብነት ቀይሮ የቡድኑን መሪነት ወደ ሦስት ከፍ አድርጓል። በኃይሉ ግቡን ካገባ በኋላ ኤሌክትሪክ የቀድሞ ክለቡ ስለነበር ደስታውን ከመግለፅ ተቆጥቧል። ጨዋታው ከቁጥጥራቸው ውጪ የሆነባቸው ኤሌክትሪኮች ጥሩ በነበሩበት ጊዜ እንኳን አስደንጋጭ ሙከራ ሳያደርጉ እጅ ሰጥተው ጨዋታውን ጨርሰዋል። ቀሪዎቹ ደቂቃዎችም ምንም ሙከራ ሳይደረግባቸው ተጠናቀዋል።

ውጤቱን ተከትሎ ነጥቡን ስምንት ያደረሰው ወልቂጤ ከተማ ከአራተኛ ደረጃ ወደ ሁለተኛ ደረጃ ሲሸጋገር ኢትዮ ኤሌክትሪክ ግን በማሟያ ውድድሩ ወደ ፕሪምየር ሊጉ የማለፍ ተስፋውን ሙሉ ለሙሉ አጨልሞ ከሜዳው ወጥቷል።