የክልል ክለቦች ሻምፒዮና የሚጀመርበት ቀን እና ቦታ ታውቋል

በኢትዮጵያ የውድድር እርከን አራተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው የክልል ክለቦች ሻምፒዮና የሚጀመርበትን ጊዜ እና ቦታ ፌዴሬሽኑ ይፋ አድርጓል።

ክልሎች እና የከተማ አስተዳደሮች የሚወክሉ ክለቦች የሚሳተፉበት እና በኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ስር የሚተዳደረው የ2013 የኢትዮጵያ ክልል ክለቦች ሻምፒዮና ውድድር በሀዋሳ እንደሚካሄድ የተገለፀ ሲሆን ከሐምሌ 18 2013 ጀምሮ ይካሄዳል ተብሏል፡፡

በውድድሩ ከየክልል ክለቦቹ ሻምፒዮን የሆኑ የወንዶች እና የሴቶች ቡድኖች ተሳታፊ የሚሆኑ ሲሆን በወንዶች እያንዳንዱ ክልል አምስት አምስት ቡድኖችን ይሳተፋል። ከአማራ፣ ኦሮሚያ፣ ደቡብ፣ ሲዳማ፣ አፋር፣ ጋምቤላ፣ ቤኒሻንጉል፣ ሶማሌ እና የሐረሪ ክልሎች እንዲሁም ከአዲስ አበባ እና የድሬዳዋ ከተማ አስተዳድር የተውጣጡ በአጠቃላይ 55 ቡድኖች ተካፋይ እንደሚሆኑም ይጠበቃል፡፡

በሴቶች ዘንድሮ ለመጀመርያ ጊዜ ውድድር እንደሚጀመር ከዚህ ቀደም መዘገባችን የሚታወስ ሲሆን ቡድኖችን የሚልኩ ክልሎች እና ከተማ መስተዳድሮች ተሳታፊ ይሆናሉ፡፡

ከፌዴሬሽኑ መረጃ በተጨማሪ አቶ ከበደ ወርቁ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የውድድር ዳይሬክተር ሀዋሳ ከተማ የተሻለ የሜዳም አቅርቦት ለክለቦቹም አማካይ ከተማ በመሆኑ እንደተመረጠች ለሶከር ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡

በወንዶቹ ውድድር ከዚህ ሸደም የነበረው አሰራር የሚቀጥል ከሆነ ስምንት ቡድኖች ወደ አንደኛ ሊግ ሲያድጉ በሴቶቹ ደግሞ ያልተገለፀ የቡድን ቁጥር ወደ ሴቶች ሁለተኛ ዲቪዝዮን የሚያድግ ይሆናል።