የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ሁለት ተጫዋቾችን ቀንሷል

በአሠልጣኝ ውበቱ አባተ የሚመራው የኢትዮጵያ ከ23 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ሁለት ተጫዋቾችን በልዩ ምክንያት ቀንሷል።

ኢትዮጵያ ለአምስተኛ ጊዜ የምታስተናግደው የምስራቅ እና መካከለኛው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ የሚካፈለው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከሰኔ 4 ጀምሮ ልምምዱን መቀመጫውን በካፍ የልዕቀት ማዕከል በማድረግ እየሰራ ይገኛል። ልምምዱን እያከናወነ የሀገር ውስጥ የአቋም መለኪያ ጨዋታዎችን እያደረገ የሚገኘው ቡድኑ አሁን በተሰማ መረጃ ሁለት ተጫዋቾችን ከስብስቡ ውጪ አድርጓል። የተቀነሱት ተጫዋቾች የግብ ዘቡ ምንተስኖት አሎ እና የአጥቂ መስመር ተጫዋቹ ይገዙ ቦጋለ ናቸው።

ሶከር ኢትዮጵያ ከቀናት በፊት በሰራችው ዘገባ የብሔራዊ ቡድኑ ተጫዋቾች የኮቪድ-19 ክትባት ማድረጋቸውን ገልፃ ነበር። ታዲያ ክትባቱ በሚሰጥበት ሰዓት ምንተስኖት አሎ እና ይገዙ ቦጋለ ‘በግል አመለካከት’ ምክንያት ክትባቱን አልወሰዱም። ከቡድኑ የአሠልጣኝ ክፍል አባላት እና ከህክምና ባለሙያዎች ክትባቱ ጎጂ እንዳልሆነ ለተጫዋቾቹ ቢነገርም ሁለቱ ተጫዋቾች አቋማቸውን ሳይቀይሩ ቀርቷል። ከዚህም መነሻነት ብሔራዊ ቡድኑ አሁን ባይሆን ወደፊት ከሀገር በሚወጣበት ሰዓት ተጫዋቾች የኮቪድ-19 ክትባት መውሰዱ ስለሚያስፈልጋቸው ስማቸው የተጠቀሰው ተጫዋቾች በወሰዱት አቋም ከስብስቡ እንዲወጡ ተደርጓል።

ሶከር ኢትዮጵያ ባገኘው መረጃ መሠረት የብሔራዊ ቡድኑ አሠልጣኝ ውበቱ አባተ እና ረዳቶቹ በነገው ዕለት በተቀነሱት ተጫዋቾች ምትክ አዲስ ጥሪ እንደሚያደርጉ ሰምተናል።