ሩዋንዳ ከሴካፋ ውድድር ራሷን አገለለች

ሐምሌ 10 በባህር ዳር በሚጀምረው የሴካፋ ከ23 ዓመት በታች ውድድር እንደሚሳተፉ ከሚጠበቁ ሀገራት አንዷ የነበረችው ሩዋንዳ እንደማትሳተፍ አስታውቃለች።

የሀገሪቱ እግርኳስ ማኅበር ከደቂቃዎች በፊት ይፋ ባደረገው መግለጫ የኮቪድ 19 ወረርሺኝ እየጨመረ በመምጣቱ ምክንያት መንግሥት ወረርሺኙን ለመቆጣጠር ያስቀመጣቸውን ገደቦች በመጥቀስ በኢትዮጵያ የሚደረገው ውድድር ላይ ብሔራዊ ቡድኑን እንደማይልክ አስታውቋል። ለሴካፋ ውሳኔውን ማሳወቁንም ጨምሮ ገልጿል።

ከብሔራዊ ቡድኑ በተጨማሪ በትናንትናው ዕለት በወጣው ዕጣ በካፍ የሴቶች ቻምፒዮንስ ሊግ የሴካፋ ዞን ማጣርያ ላይ በምድብ ሐ ተደልድሎ የነበረው ስካንዲኔቪያ ሴቶች ቡድንም እንደማይሳተፍ ተረጋግጧል።

ቀድሞውንም ከአባል ሀገራት ዘግይታ ተጫዋቾቿን በመጥራት ዝግጅት ጀምራ የነበረችው ሩዋንዳ ከሱዳን እና ተጋባዧ ዲሞክራቲክ ኮንጎ በመቀጠል ሦስተኛዋ ራሷን ከውድድሩ ያገለለች ሀገር ሆናለች። በዚህም አሁን ባለው ሁኔታ ውድድሩ በ10 ሀገራት መካከል እንደሚደረግ ይጠበቃል።