የማሟያ ውድድሩ የመጨረሻ መርሐ-ግብር የሆነው የሀምበሪቾ እና ኤሌክትሪክ ጨዋታ አራት ግቦች ተቆጥረውበት በኢትዮ ኤሌክትሪክ 3-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።
ለአዳማ ከተማ ሦስት ነጥብ አስረክበው ለዛሬው ጨዋታ የቀረቡት ሀምበሪቾዎች አራት ለውጥ በማድረግ ጨዋታውን ጀምረዋል። በዚህም አሠልጣኝ ግርማ ታደሠ ሮቦት ሰለሎ፣ ዋቁማ ዲንሳ፣ ዳግም በቀለ እና አቤኔዘር ኦቴን አሳርፈው ብሩክ ኤልያስ፣ በረከት ወንድሙ፣ ፀጋአብ ዮሴፍ እና ነጋሽ ታደሠን ወደ ሜዳ አስገብተዋል። በተቃራኒው በአራተኛ ዙር ጨዋታ በወልቂጤ ከተማ ሦስት ለምንም የተረታው የአሠልጣኝ ክፍሌ ቦልተና ስብስብ ደግሞ አዲስ ነጋሽ፣ አቅሌሲያ ግርማ፣ ሳሙኤል ታዬ እና እንዳለ ዘውገን አስወጥቶ ስንታየሁ ዋለሜ፣ ሚካኤል ለማ፣ ኤርሚያስ ኃይሉ እና ብሩክ ጌታቸው ቋሚ አሰላለፍ ውስጥ አካቷል።
የጨዋታውን የሀይል ሚዛን ወደ ራሳቸው አድርገው መጫወት የጀመሩት ሀምበሪቾዎች የውድድሩን የመጀመሪያ ነጥባቸውን በዚህ የመጨረሻ ጨዋታ ለማግኘት ጠንክረው ሲጫወቱ ታይቷል። በዚህም በጨዋታው ሩብ ደቂቃ ላይ ከቅጣት ምት የተሻገረን ኳስ የኢትዮ ኤሌክትሪክ ተከላካዮች በሚገባ ማፅዳት ተስኗቸው አምረላ ደልታታ አግኝቶት ግብ ሊያስቆጥር ተቃርቦ ነበር። ነገርግን አምረላ በማይመች ሁኔታ ውስጥ ሆኖ ወደ ግብ የመታውን ኳስ የግብ ዘቡ ቢኒያም ታከለ አድኖታል። ከሁለት ደቂቃዎች በኋላም ቢኒያም ጌታቸው ሌላ እጅግ ለግብ የቀረበ ኳስ አግኝቶ የነበረ ቢሆንም ሞክሼው ግብ ጠባቂ ኳሱን በድጋሜ በጥሩ ቅልጥፍና አምክኖታል።
በኳስ ቁጥጥሩ ረገድ እየተሻሻሉ የመጡት ኢትዮ ኤሌክትሪኮች በበኩላቸው እስከ 34ኛው ደቂቃ ድረስ አንድም የጠራ የግብ ማግባር ሙከራ ሳይደርጉ ጨዋታው ቀጥሏል። እርግጥ በ32ኛው ደቂቃ በተደራጀ መልኩ ወደ ሀምበሪቾ የግብ ክልል ያመሩ ቢሆንም የፈጠሩትን ወርቃማ ዕድል ሳይጠቀሙበት ተመልሰዋል። በ34ኛው ደቂቃ ግን የጫላ ተሺታን ጉዳት ተከትሎ ተቀይሮ የገባው አደም አባስ ከቀኝ መስመር የተሻገረለትን ኳስ በግንባሩ ቢሞክረውም ለጥቂት ወጥቶበታል። ሙሉ የመጀመሪያው አጋማሽ ተጠናቆ በተጨመሩት ሁለት ደቂቃዎች አጋማሽ ላይ ፀጋአብ ዮሴፍ ከሳጥን ውጪ በመታው ኳስ ቡድኑን መሪ ለማድረግ ጥሮ ወጥቶበታል። አጋማሹም ያለ ጎል ተጠናቋል።
ሁለተኛው አጋማሽ እንደተጀመረ አስደንጋጭ ሙከራዎችን ማድረግ የጀመሩት ኤሌክትሪኮች ገና በአጋማሹ ጅማሮ መሪ ለመሆን መልፋት ይዘዋል ። በተለይ አሠልጣኙ ቀይረው ያስገቧቸው ተጫዋቾች ሀምበሪቾዎችን ሲያስጨንቁ ታይቷል። በመጀመሪያም ፀጋ ደርቤ ግብ ጠባቂው እሸቴ ተሾመ የግብ ክልሉን ለቆ ሲወጣ ወደ ጎል የመታው ኳስ በተከላካይ ሲመለስ በመቀጠል ደግሞ ስንታየሁ ዋለጬ ከሳጥን ውጪ አክርሮ ወደ ጎል የላከው ኳስ ለጥቂት ወደ ውጪ ወጥቷል። 50ኛው ደቂቃ ላይ ግን የአሠልጣኙ የተጫዋች ለውጥ ፍሬ አፍርቶ ኤሌክትሪክ መሪ ሆኗል። በዚህም ሜካኤልን ቀይሮ የገባው ሳሙኤል ታዬ ሳጥን ጫፍ ሆኖ የመታት ኳስ መረብ ላይ አርፋለች።
አሁንም ጫና ማሳደራቸውን የቀጠሉት ኤሌክትሪኮች በ58ኛው ደቂቃ የግቡ ባለቤት ሳሙኤል ለስንታየሁ በአስደናቂ ሁኔታ አቀብሎት ስንታየሁ ባመከነው ኳስ መሪነታቸውን ወደ ሁለት ከፍ ለማድረግ ሞክረዋል። ወደ ጨዋታው ለመመለስ የሚያስችላቸውን ጎል መፈለግ የጀመሩት ሀምበሪቾዎች በበኩላቸው አምረላ ደልታታ የግል ጥረቱን ተጠቅሞ ወደ ሳጥን ባሻማው እና ብሩክ ኤልያስ ወደ ግብ በሞከረው ኳስ አቻ ሊሆኑ ነበር።
የሀምበሪቾዎች ግብ ለማስቆጠር ነቅሎ መውጣት የጠቀማቸው ኤልፓዎች በ66ኛው እና በ67ኛው ደቂቃ ተከታታይ ሙከራዎችን አድርገው ነበር። በቅድሚያ ኤርሚያስ በቀኝ መስመር የሞከረው ኳስ የግቡን መረብ ታኮ ሲወጣ ሁለተኛው ሙከራ ግን መረብ ላይ አርፏል። በዚህም በተቃራኒ አቅጣጫ (በግራ መስመር) ከተከላካዮች ጀርባ አፈትልኮ የወጣው ፀጋ ደርቤ በጥሩ አጨራረስ ለቡድኑ ሁለተኛ ጎል አስቆጥሯል። ጨዋታው ከቁጥጥራቸው እየወጣ የመጣው ሀምበሪቾዎች ሁለተኛውን ግብ ካስተናገዱ ከደቂቃ በኋላ በቢንያም ጌታቸው አማካኝነት ሙከራ ቢያደርጉም ዛሬ ጥሩ የነበረው የኤሌክትሪክ የኋላ መስመር ኳሱ ወደ ግብነት እንዳይቀየር አድርጎታል።
በሁለተኛው አጋማሽ እጅግ ተሻሽለው የቀረቡት ኤሌክትሪኮች በ80ኛው ደቂቃ ላይም በቁጥር በዝተው የተጋጣሚ የፍፁም ቅጣት ምት ክልል ውስጥ በመገኘታቸው ሦስተኛ ጎል አስቆጥረዋል። በዚህም ቡድኑ በቀኝ መስመር የተገኘውን ኳስ በሩቁ ቋሚ ሆኖ ሲጠብቅ የነበረው ሳሙኤል ለራሱ ሁለተኛ ለቡድኑ ደግሞ ሦስተኛ ጎል አስቆጥሯል። ሙሉ የጨዋታ ክፍለ ጊዜው ሊጠናቀቅ አምስት ደቂቃዎች ሲቀሩት ደግሞ ሀምበሪቾዎች የማስተዛዘኛውን ጎል በሙሉነህ ገብረመድህን አማካኝነት አግኝተዋል። በቀሪ ደቂቃዎችም ተጨማሪ ጎል ሳይቆጠር ጨዋታው ተጠናቋል።
የውድድሩ ወዳቂ መሆናቸውን ቀድመው ያወቁት ኢትዮ ኤሌክትሪኮች እና ሀምበሪቾ ዱራሜዎች የደረጃ ሰንጠረዡን ግርጌ በ6 እና 0 ነጥቦች ይዘው በቅደም ተከተል አምስተኛ እና ስድስተኛ ሆነው ውድድራቸውን ጨርሰዋል። ከሰኔ 18 ጀምሮ ሲደረግ የነበረው የማሟያ ውድድርም አዳማ ከተማ፣ ወልቂጤ ከተማ እና ጅማ አባጅፋርን አላፊ አድርጎ ፍፃሜውን አግኝቷል።