አስቻለው ታመነ ቻምፒዮኖቹን ለመቀላቀል ከጫፍ ደርሷል

የአሠልጣኛቸውን ውል ካደሱ በኋላ በዝውውር ገበያው ላይ እየተሳተፉ የሚገኙት ዐፄዎቹ የመሐል ተከላካይ ለማስፈረም የመጨረሻ ደረጃ ላይ ደርሰዋል።

የ2013 የኢትዮጵያ ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ አሸናፊው ክለብ ፋሲል ከነማ የአሠልጣኝ ሥዩም ከበደን ውል ለአንድ ዓመት ማራዘሙን መዘገባችን ይታወሳል። ከዛም ክለቡ ፊቱን ወደ ተጫዋቾች ዝውውር በማድረግ የቅዱስ ጊዮርጊሱን የቀኝ መስመር ተከላካይ አብዱልከሪም መሐመድን ወደ ስብስቡ በመቀላቀል ዝውውሩን “ሀ” ብሎ ጀምሯል። ሶከር ኢትዮጵያ አሁን ባገኘችው መረጃ ደግሞ ፋሲሎች ሌላኛውን የቅዱስ ጊዮርጊስ የተከላካይ መስመር ተጫዋች የግላቸው ለማድረግ ከጫፍ ደርሰዋል።

ፋሲል ከነማን ለማገልገል ከጫፍ የደረሰው ተጫዋች አስቻለው ታመነ ነው። በዲላ ከተማ የእግር ኳስ ህይወቱን የጀመረው የመሐል ተከላካዩ ደደቢትን ለቆ በ2007 ክረምት ላይ ነበር ቅዱስ ጊዮርጊስን ተቀላቅሎ ለፈረሰኞቹ ግልጋሎት መስጠት የጀመረው። ለሰባት ዓመታትም በአንጋፋው ክለብ በመቆየት ምርጥ ብቃቱን አሳይቶ ነበር። ነገርግን በዘንድሮ የውድድር ዘመን ክለቡ ተጫዋቹ ላይ “የዲሲፕሊን ጥሰት” እግድ አስተላልፎበት እንደነበረም አይዘነጋም። የሆነው ሆኖ ቀልጣፋው የመሐል ተከላካይ የጃኖ ለባሾቹን መለያ ለማድረግ በትናንትናው ዕለት ከክለቡ አመራሮች ጋር በስካይ ላይት ሆቴል ድርድር ማድረጉን ሶከር ኢትዮጵያ አውቃለች። 

ተጫዋቹ እና ክለቡ በበርካታ ጉዳዮች ላይ ከስምምነት መድረሳቸው ሲታወቅ ምናልባታ ተጫዋቹ እንዲፈፀምለት የጠየቀው ቅድመ ሁኔታ በዛሬው ዕለት ተግባራዊ ከሆነ ፊርማውን እንደሚያኖር ይጠበቃል። ሶከር ኢትዮጵያም ጉዳዩን እየተከታተለች የሚወጡ አዳዲስ መረጃዎችን የምታቀርብ ይሆናል።