ዋልያው የመጨረሻ ልምምዱን ዛሬ ሰርቷል

ነገ ከኤርትራ ብሔራዊ ቡድን ጋር የሴካፋ የመክፈቻ ጨዋታውን የሚያደርገው የኢትዮጵያ ከ23 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን የመጨረሻ ልምምዱን ከሰዓት አከናውኗል።

በአሠልጣኝ ውበቱ አባተ የሚመራው የኢትዮጵያ ከ23 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን በነገው ዕለት የሚጀመረው የምስራቅ እና መካከለኛው የአፍሪካ ዋንጫ ውድድር ከመጀመሩ በፊት የመጨረሻ ምዕራፍ ልምምዱን በባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም አከናውኗል። ነገ ጨዋታው በሚደረግበት ሰዓት (9:00) ልምምድ መስራት የጀመረው ብሔራዊ ቡድኑም በቅድሚያ ቀለል ያሉ የማፍታቻ እንቅስቃሴዎችን ሲያደርግ አስተውለናል።

የማላቀቂያ እና የማፍታቻ እንቅስቃሴዎቹ ከተከናወኑ በኋላ ደግሞ የአሠልጣኝ ቡድን አባላቱ ተጫዋቾችን የቆመ ኳስ አጠቃቀም ሲያሰሩ አይተናል። በተለይ በተጋጣሚ የግብ ክልል አካባቢ በሚገኙ ቦታዎች ላይ የቅጣት ምቶችን የቡድን ሥራ በታከለበት አጨዋወት ወደ ግብነት ለመቀየር ሲሰራ ነበር። የመዓዘን ምቶችም ሲገኙ ኳሶች በቀጥታ ከመሻማታቸው በተጨማሪ በአንድ ሁለት ቅብብል ወደ ግብ እንዲደርሱ ሲሰራ አይተናል። ተጫዋቾቹ ለአንድ ሰዓት የተጠጋ ደቂቃዎችን ከተለማመዱ በኋላ በአሠልጣኝ ውበቱ አባተ ምክር ሲለገሳቸው ሰምተናል።

በትናንቱ ዘገባችን ከነገው ጨዋታ ውጪ እንደሆነ የገለፅነው መስፍን ታፈሰ ከብሔራዊ ቡድኑ የአካል ብቃት አሠልጣኝ ዶ/ር ዘሩ በቀለ ጋር በመሆን በተናጥል ቀለል ያሉ ልምምዶችን ሲሰራ ታዝበናል። 10 ሰዓት ሲልም ተጫዋቾቹ በተዝናና መንገድ የዕለቱን ልምምድ አጠናቀው ከሜዳ ወጥተዋል።

የተጫዋቾቹ ልምምድ ከተጠናቀቀ በኋላ የብሔራዊ ቡድኑ የአሠልጣኝ ክፍል አባላት በሩብ ሜዳ በአራት ተከፋፍለው አዝናኝ ጨዋታ ሲያደርጉ አስተውለናል። ዋናውን አሠልጣኝ ውበቱ አባተን ጨምሮ ሌሎች የአሠልጣኝ ክፍል አባላትን ያካተተውን አዝናኝ የእርስ በእርስ ጨዋታንም ተጫዋቾች በአድናቆት ሲመለከቱ አስተውለናል።

የነገ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተጋጣሚ የሆነችው ኤርትራ ዋልያዎቹ ልምምድ ከመስራታቸው 30 ደቂቃዎች አስቀድሞ ልምምዳቸውን በባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም አከናውነው ወጥተዋል። የውድድሩ የመክፈቻ ጨዋታ የሆነው የኢትዮጵያ እና ኤርትራ ከ23 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድኖች ጨዋታም ነገ 9:00 የሚጀመር ይሆናል።