የአሠልጣኞች አስተያየት | ኢትዮጵያ 3-3 ኤርትራ

የሴካፋ የመክፈቻ መርሐ-ግብር የሆነው የኢትዮጵያ እና ኤርትራ ጨዋታ በአቻ ውጤት ከተጠናቀቀ በኋላ የሁለቱ ቡድን አሠልጣኞች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

ውበቱ አባተ – ኢትዮጵያ

ጨዋታው ምን መልክ ነበረው?

ይህ የመጀመሪያ ጨዋታችን ነው። እንደ መጀመሪያ ጨዋታ ያገኘነው የአቻ ውጤት መጥፎ አይደለም። በጨዋታው ግን ብዙ የግብ ማግባት አጋጣሚዎችም ፈጥረን ነበር። በዚህም ሦስት ጎሎችን አስቆጥረናል። ነገርግን መጥፎው ነገር ሦስት ግቦችን አስተናግደን ነበር። የሆነው ሆኖ በጨዋታው ድክመታችን ምን እንደሆነ አይተናል። በድክመታችን ላይም ሰርተን በቀጣይ ጨዋታ ጠንክረን ለመቅረብ እንሞክራለን።

በጨዋታው ግቦች በርክተው ነበር። ይህ ከምን የመጣ ነው?

እነሱ ያገቡብን ጎሎች ተመሳሳይ መንገድ ነበራቸው። እነርሱም በመልሶ ማጥቃት የተገኙ ናቸው። ከዚህ ውጪ በረጅም የሚጣሉ ኳሶችንም ለመጠቀም ሲጥሩ ነበር። በዋናነት ደግሞ ዓሊ ሱሌይማንን መሠረት ያደረገ አጨዋወት ሲከተሉ ነበር። በዚህ ሂደት ግቦችን ከማስቆጠር በተጨማሪ ሌሎችንም የግብ ዕድሎች መፍጠር ችለዋል። ምናልባት ግን ሁለቱም ሀገሮች አንድ ሀገር የነበሩ መሆኑ ፉክክሩ ትንሽ ጠንከር እንዲል ያደረገው ይመስለኛል። በአጠቃላይ ክፍት ጨዋታ ነበር። ለዛም ነው ስድስት ጎሎች የተቆጠሩት።

በጨዋታው ስለነበረው የመከላከል ችግር? እና ቶሎ ለውጥ ስላልተደረገበት ምክንያት…?

ከመጀመሪያው ደቂቃ ጀምሮ ክፍተቱ ነበር። ግን ክፍተት ባየህ ቁጥር አስራ አንድ ተጫዋች መቀየር አትችልም። የትኛው የሜዳ ክፍል ላይ የበለጠ ክፍተት ነበረ የሚለውን ለማየት ሞክረናል። የተከላካይ ክፍሉ የተሻለ የራስ መተማመኑ እንዲጎለብት ነበር ጊዜ የሰጠነው። ኋላ ላይ ግን ችግሩ ባለመቀረፉ በቦታው ላይ ተጫዋች ለውጠናል።

ቡድኑ ላይ ስላየው ተስፋ?

ቡድን በአንድ ጊዜ አይገነባም። ተጫዋቾቹ ለአንድ ወር ነው የተለማመዱት። እንዳልኩት ደግሞ ቡድን በሂደት ነው የሚገነባው። እርግጥ ተጫዋቹን በክለቦቻቸው ሲጫወቱ እናቃቸዋለን። ግን እነርሱን አሰባስቦ አንድ አድርጎ ማጫወት ደግሞ ጊዜ ይፈልጋል። ወደፊት ግን ጥሩ ተስፋ ያለ ይመስለኛል።

ስለ ኤርትራ ብሄራዊ ቡድን ጥንካሬ?

ጠንካራ የተከላካይ ክፍል አላቸው። የአየር ኳስ ላይም ጥሩ ናቸው። ከዚህ ውጪ ቅድም የገለፅኩት የመልሶ ማጥቃታቸውም ስል ነበር። ምናልባት ግን አጨራረስ ላይ የተሻሉ ቢሆኑ ከዚህም በላይ ሊያገቡ ይችሉ ነበር።

ዳንኤል ዮሐንስ – የኤርትራ ብሔራዊ ቡድን ቴክኒካል ዳይሬክተር

ስለ ጨዋታው?

ቡድናችን ታክቲካሊ ዲሲፕሊንድ ነበር። በጠንካራ ጎናችን ላይም ያሳየነው እንቅስቃሴ የሚደነቅ ነበር። በጨዋታው የመጀመሪያ ደቂቃዎች ላይም ከእነርሱ ቀድመን መሪ የምንሆንበትን ዕድሎች ፈጥረን ነበር። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በጨዋታው የመከላከል ክፍተት ነበረበት። በተለይ ከማጥቃት ወደ መከላከል የሚደረግ ሽግግር ላይ ድክመት ነበር። ይሄንን የተጋጣሚ ክፍተት ለመጠቀምም የመልሶ ማጥቃት አጨዋወትን ተግባራዊ አድርገን ተጫውተናል። በዚህም ሦስት ጎሎችን አስቆጥረናል። ከምንም በላይ ግን ታክቲካል ዲሲፕሊናችን ጥሩ ነበር።

በጨዋታው ላይ ሲከተሉት ስለነበረው አጨዋወት?

ቅድም እንዳልኩት ተጫዋቾቹ ይዘውት ወደ ሜዳ በገቡት ነገር ላይ በትልቅ ተጋድሎ ሲጫወቱ ነበር። ከዚህ በተጨማሪ የተጋጣሚን ድክመትም ለመጠቀም ተፈልጎ ነበር። ከምንም በላይ ግን ተጫዋቾቻችን ጨዋታውን በማንበቡ እና እርጋታ በተሞላበት መንገድ በጥሩ የራስ መተማመን በመጫወቱ ረገድ እጅግ ጥሩ ነበሩ።

ስለ ተጋጣሚያቸው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን እንቅስቃሴ?

ቡድኑ ጥሩ ቡድን ነበር። ግን የተከላካይ ክፍሉ ላይ ክፍተት አይቻለሁ። ኳሱን በማንሸራሸሩ ረገድ እና ቅርፅ ባለው መንገድ ሲጫወቱ ጥሩ ነበሩ። በአጠቃላይ ቡድኑ ጥሩ ቢጫወትም ሰብሮ ወደ ተጋጣሚ ሳጥን በመግባቱ በኩል ችግር ነበረበት። በአንድ አጥቂ ላይ ብቻ ነበር ተንጠልጥሎ ሲጫወት የነበረው።

ጨዋታው አቻ ስለመጠናቀቁ?

ጨዋታው 3 አቻ አልቋል። ግን ሁለቱም ብሔራዊ ቡድኖች ከጨዋታው በላይ የተጠቀሙ ይመስለኛል። እንደምታውቁት ሁለቱ ቡድኖች ረጅም ጊዜ ሆኗቸዋል የእርስ በእርስ ጨዋታ ካደረጉ። እኛ ያስቆጠርናቸውን ሦስት ጎሎች ለአብሮነታችን እና ለመከባበራችን ይሁን ብለናል። በአጠቃላይ እንዳልኩት ግን የሁለቱ ብሔራዊ ቡድኖች ጨዋታ ከጨዋታም በላይ ነበር።