ተስፈኛው ወጣት ተጫዋች ውሉን አድሷል

በፋሲል ከነማ ቤት በተሰለፈባቸው ጨዋታዎች ግቦችን እና ለግብ የሚሆኑ ኳሶችን ሲያመቻች የነበረው ናትናኤል ገብረጊዮርጊስ ውሉን አራዝሟል።

የ2013 የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የዋንጫ ባለቤት በመሆን በካፍ የቻምፒየንስ ሊግ ውድድር ላይ የሚሳተፈው ፋሲል ከነማ በአዲስ መልክ አስቻለው ታመነን፣ ኦኪኪ አፎላቢ እና አብዱልከሪም መሐመድን ማስፈረሙ ይታወቃል። ከአዲስ ተጫዋቾቹ በተጨማሪ የዳንኤል ዘመዴ፣ ኪሩቤል ኃይሉ፣ የማሊ ዜግነት ያለውን ግብ ጠባቂ ሚኬል ሳማኪን እና የተከላካዩን ከድር ኩሊባሊን ውል ደግሞ ማራዘሙ ይታወሳል፡፡ ዛሬ በተሰማ የክለቡ ዜና ደግሞ ናትናኤል ገብረጊዮርጊስ ውል ማደሱን ሶከር ኢትዮጵያ ከክለቡ አረጋግጧል።

ከፋሲል ከነማ ተስፋ ቡድን የተገኘው ናትናኤል ገብረጊዮርጊስ በ2013 ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ጥሩ ውድድር ጊዜ ያሳለፈ ሲሆን በወጣቶች ኮኮብ ተጫዋች ምርጫ ላይም እጩ ነበር። ከዚህ በተጨማሪ ተጫዋቹ በርካታ ጨዋታዎች ላይ በመሰለፍ ለቡድኑ ወሳኝ ነጥቦችን ያስገኘው ሲሆን ከሌሎች ክለቦች የእናስፈርምህ ጥያቄ ቢቀርብለትም ያሳደገውን ክለብ በመምረጥ ለተጨማሪ ሦስት ዓመታት ከሻምፒዮኖቹ ጋር የሚያቆየውን ውል ፈርሟል።