ወልቂጤ ከተማ ከአሰልጣኙ ጋር አብሮ ይቀጥላል

በፕሪምየር ሊጉ የመቆየትን ዕድል በእጁ ያስገባው ወልቂጤ ከተማ ከአሰልጣኙ ጋር አብሮ እንደሚቆይ ታውቋል።

የዘንድሮውን የውድድር ዓመት ከጀመረበት የተነቃቃ አኳኋን አንፃር ባልተጠበቀ መልኩ በወራጅነት ያጠናቀቀው ወልቂጤ ከተማ በቀጣይ ዓመት የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የትግራይ ክልል ክለቦችን ቦታ ለሟሟላት በተደረገው ውድድር ላይ ባስመዘገበው ውጤት በሀገሪቱ የመጀመሪያው የሊግ ዕርከን የመቀጠል ዕድልን አሳክቷል። በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን ከደግአረገ ይግዛው ጋር ከተለያየ በኋላ በረዳት አሠልጣኝ አብዱልሀኒ ተሰማ እና ሲሳይ አብርሃም የተመራው ክለቡ ከፕሪምየር ሊጉ መውረዱ የሚታወስ ሲሆን የትግራይ ክልል ክለቦች ካልተሳተፉ ለመተካት በተደረገው ውድድር ላይ ጳውሎስ ጌታቸው ቡድኑን እየመሩ ሁለተኛ ደረጃ ይዞ በማጠናቀቅ በፕሪምየር ሊጉ እንደሚቆይ አረጋግጧል።

ይህን ውጤት ያስመዘገበበት የሀዋሳው ውድድር ከመጀመሩ አስቀድሞ ክለቡ የቀድሞ የኢትዮጵያ ቡና፣ ሀዲያ ሆሳዕና እና ባህር ዳር ከተማ አሰልጣኝ ጳውሎስ ጌታቸው ከጅማ አባ ጅፋር ጋር በውድድር ዘመኑ አጋማሽ ከተለያዩ ጥቂት ወራት በኋላ ወልቂጤን በመለያ ውድድሩ ወቅት መረከባቸው የሚታወስ ነው።

ሶከር ኢትዮጵያ ዛሬ ባገኘችው መረጃ መሰረትም በውድድሩ በተመዘገበው ውጤት ደስተኛ የሆኑት የወልቂጤ ከተማ አመራሮች አሠልጣኝ ጳውሎስ ጌታቸው ለከርሞው ቡድኑን ይዘው እንዲቆዩ ከወሳኔ ላይ ደርሰዋል። በዚህም ክለቡ እና አሠልጣኙ ለቀጣይ አንድ ዓመት አብረው ለመስራት የሚያበቃቸውን ዉል ማሰራቸው ተሰምቷል። በቀጣይ ቀናት ክለቡ በአሰልጣኝ ጳውሎስ ስር ለሚገነባው ቡድን ተፈላጊ ተጫዋቾችን ለመሸመት ወደ ገበያ እንደሚወጣም ይጠበቃል።