ሀዲያ ሆሳዕና ላይ የዲሲፕሊን ውሳኔ ተላልፏል

ዘንድሮ ከውዝግቦች ጋር ስሙ የማይጠፋው ሀዲያ ሆሳዕና በኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የዲሲፕሊን ኮሚቴ ውሳኔ ተላልፎበታል።

አሠልጣኝ አሸናፊ በቀለን ከወራት በፊት ከክለቡ ያሰናበተው ሀዲያ ሆሳዕና በአሠልጣኙ ክስ ተመስርቶበት እንደነበረ ይታወሳል። ያለ አግባብ ውል እያለኝ ደሞዜ አልተከፈለኝም ያሉት አሠልጣኙም ጉዳያቸው በኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የዲሲፕሊን ኮሚቴ እንዲታይ የክስ አቤቱታ አስገብተው በዛሬው ዕለት ምላሽ አግኝተዋል። ኮሚቴው በወሰነው ውሳኔ መሠረትም አሠልጣኙ ውድድር አልመራም ያሉበት ምክንያት ለውድድር ያሚያበቁ ተጫዋቾች ያለመኖራቸው፣ 15 ተጫዋቾች ለመጫወት ፍቃደኛ ባለመሆናቸው፣ 5 ወራት የተቀጣ ተጨዋች ማጫወት ከሙያ አኳያ በአሰልጣኝነታቸው መዝነው ውሳኔ መስጠት ያለባቸው በመሆኑ ከስራ የሚያሰናብታቸው ጥፋት ፈጽመዋል ለማለት አይቻልም ብሏል። በሌላ በኩል በተከራካሪዎች መካከል በተፈረመው ውል አንቀጽ አራት ውል የሚቋረጠው በስምምነት፣ የውል ጊዜው ሲያበቃ መሆኑ ተወስቶ ሀዲያ ሆሳዕና እግር ኳስ ክለብ ከሚያዚያ ወር እስከ ሰኔ ወር 2013 ዓ.ም ለአሠልጣኝ አሸናፊ በቀለ ያልከፈለውን ደመወዝ እንዲከፍል ተወስኗል።

ክለቡ ክፍያውን ይህ ውሳኔ በደረሰው በ7 ቀናት ውስጥ እንዲፈጽም ተጠይቆ በ7 ቀናት ውሰጥ ክፍያውን ካልፈፀመ ግን ክለቡ ከፌዴሬሽኑ ምንም አይነት አገልግሎት እንዳያገኝ እንዲሁም ከፕሪምየር ሊግም ሆነ ከማንኛውም የእግር ኳስ ውድድር እንዲታገድ ተወስኗል፡፡ የዲሲፕሊን ኮሚቴ ባስተላለፈው ውሳኔ ላይም ክለቡ ይግባኝ ማለት መብቱ እንደሆነ አመላክቷል።

ሙሉ የውሳኔ ደብዳቤው ከስር ተያይዟል👇