የወጣቱ ግብ ጠባቂ ዝውውር ተጠናቀቀ

በቅርቡ ወደ ባህር ዳር ከተማ እንደሚያመራ ዘግበን የነበረው የወጣቱ ግብ ጠባቂ አቡበከር ኑሪ ዝውውር በዛሬው ዕለት ተጠናቋል፡፡

በቅርቡ ሶከር ኢትዮጵያ በዘገባዋ ወጣቱ ግብ ጠባቂ አብበከር ኑሪ ወደ ባህርዳር ከተማ ሊያመራ ከጫፍ መድረሱን የዘገብን ሲሆን በዛሬው ዕለት ደግሞ የተጫዋቹ ዝውውር ተጠናቋል፡፡ እግር ኳስን በመቱ ከተማ በክለብ ደረጃ በመጫወት የጀመረው እና በክለቡም ሶስት የውድድር ዓመትን ያሳለፈው ተጫዋቹ በመቀጠል 2012 መስከረም ወር መግቢያ ወደ ወሎ ኮምቦልቻ አምርቶ እስከ አጋማሹ ድረስ በክለቡ ቆይታን አድርጓል፡፡

በተሰረዘው የውድድር ዓመት መጋቢት ወር ጅማ አባጅፋርን የተቀላቀለው ተስፈኛው ግብ ጠባቂ ዘንድሮ በኢትዮጵያ ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ላይ ምንም እንኳን ክለቡ አባጅፋር በውጤት የታጀበ ዓመትን ማሳለፍ ባይችልም አቡበከር በግሉ ድንቅ ዓመት በማሳለፍ ከበርካቶች አድናቆትን አግኝቷል፡፡ ይህን ተከትሎም አመሻሽ ላይ የጣና ሞገዶቹ አምስተኛ ፈራሚ ሆኖ ወደ ክለቡ ተቀላቅሏል፡፡