ወላይታ ድቻ ሦስት ተጫዋቾችን አስፈርሟል

ዘግይቶ ወደ ዝውውሩ የገባው ወላይታ ድቻ ሦስት ተጫዋቾችን ወደ ስብስቡ ቀላቅሏል።

በ33 ነጥቦች ስምንተኛ ደረጃን ይዞ ያጠናቀቀው ወላይታ ድቻ የዝውውር መስኮቱ በሐምሌ ወር መጀመሪያ ከተከፈተ በኋላ ዝምታን መርጦ መክረሙ ይታወሳል። ሰሞኑን ከተኛበት የነቃው ክለቡ ውል ያለቀባቸውን ተጫዋቾች እንዲሁም አዳዲስ ተጫዋቾችን ወደ ክለቡ መቀላቀል ይዟል።

ከደቂቃዎች በፊት ቡድኑን ከተቀላቀሉት ተጫዋቾች መካከል የመስመር ተከላካዩ ዘካሪያስ ቱጂ አንዱ ነው። የቀድሞ የቅዱስ ጊዮርጊስ እና ብሔራዊ ቡድን ተጫዋች ከፈረሰኞቹ ከተለያየ በኋላ በቅዱስ ጊዮርጊስ ቆይታ ያደረገ ሲሆን የተጠናቀቀው የውድድር ዓመትን በኢትዮጵያ ቡና አሳልፎ በአንድ ዓመት ውል ወደ ድቻ አምርቷል።

አማካዩ ንጋቱ ገብረሥላሴ ሌላው ፈራሚ ነው። በጅማ አባ ጅፋር ረጅም ጊዜ ያሳለፈው ተጫዋቹ ከቡድኑ ጋር ወደ ፕሪምየር ሊግ ከማደጉ ባሻገር የሊጉን ዋንጫ ሲያነሱም አባል የነበረ ሲሆን በተጠናቀቀው የውድድር ዓመትም ከጥቂት ጨዋታ በቀር በአብዛኛዎቹ ተሰልፎ ተጫውቷል።

የአጥቂ መስመር ተጫዋቹ ምንይሉ ወንድሙ ሦስተኛው ፈራሚ ነው። የቀድሞ የመከላከያ አጥቂ ባለፈው ክረምት ወደ መቐለ አምርቶ የነበረ ቢሆንም ክለቡ በሊጉ ባለመሳተፉ ወደ ባህር ዳር አቅንቶ የውድድር ዘመኑን ያሳለፈ ሲሆን ቀጣዩን ዓመት በጦና ንቦቹ ቤት ለማሳለፍ በአንድ ዓመት ውል አምርቷል።