ሴቶች ፕሪምየር ሊግ | ድሬዳዋ ከተማ ሁለት አዳዲስ ተጫዋቾችን አስፈረመ

ባጣቸው በርካታ ተጫዋቾችን ምትክ ከሰሞኑ አዳዲስ ተጫዋቾችን ወደ ስብስቡ እየቀላቀለ የሚገኘው ድሬዳዋ ከተማ ትናንት አመሻሽ ሁለት ተጨማሪ ተጫዋቾችን አስፈርሟል፡፡

ግብ ጠባቂዋ ብርሀን ባልቻ ወደ ድሬዳዋ አምርታለች፡፡ ከሻሸመኔ ከተማ ሀዋሳን ከተቀላቀለች በኋላ የተጠናቀቀውን የውድድር ዘመን በሀዋሳ በተጠባባቂ ግብ ጠባቂነት ያሳለፈችው ተጫዋቿ በሁለት ዓመት ውል ለድሬዳዋ ፊርማዋን አኑራለች፡፡

ፈጣኗ አጥቂ ቤተልሄም ታምሩ የምስራቁን ክለብ የተቀላቀለች አስራ አንደኛ አዲስ ፈራሚ ተጫዋች ሆናለች፡፡ ከአርባምንጭ ከተማ የተገኘችው የቀድሞዋ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የአጥቂ ስፍራ ተጫዋች የ2013 የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግን በአዲስ አበባ ከተማ ተጫውታ ካሳለፈች በኃላ የአሰልጣኝ ብዙአየው ጀምበሩን ክለብ ተቀላቅላለች፡፡