የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለአንድ ተጫዋች ጥሪ አድርጓል

ለዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ዝግጅቱን ዛሬ የጀመረው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለአንድ ተጫዋች ጥሪ ማቅረቡ ታውቋል።

ከቀናት በፊት ለ28 ተጫዋቾች ጥሪ በማቅረብ ለዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዎች ለመዘጋጀት እንቅስቃሴ የጀመረው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በትናንትናው ዕለት አማካዩ ሀይደር ሸረፋ እና አጥቂው ሙጂብ ቃሲምን በግል ጉዳይ ምክንያት ከስብስቡ ውጪ እንዳደረገ ዘግበን ነበር። በተቀነሱት ተጫዋቾች ምትክ አዲስ ተጫዋች እንደሚጠሩ ሲጠበቁ የነበሩት አሠልጣኝ ውበቱ አባተም በዛሬው ዕለት ለመስመር አጥቂው ቸርነት ጉግሳ ጥሪ ማቅረባቸው ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች።

በ28 ተጫዋቾች ዝርዝር ውስጥ ስሙ ያልነበረው ቸርነት ዛሬ እንደ አዲስ ጥሪ ከደረሰው በኋላ ከስብስቡ ጋር ወደ አዳማ እናዳቀና ለማወቅ ችለናል። የቸርነትን ወደ ስብስቡ መካተትን ተከትሎም ሁለቱ ወንድማማቾች (ቸርነት እና ሽመክት) በብሔራዊ ቡድኑ አጋር የሚሆኑበት ዕድል ተፈጥሯል።