መከላከያ የአማካይ ስፍራ ተጫዋች አስፈርሟል

በኢትዮጵያ ቡና የውድድር ዓመቱን ያገባደደው የአማካይ መስመር ተጫዋች ቀጣይ ማረፊያው መከላከያ መሆኑ እርግጥ ሆኗል።

በአሠልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ እየተመሩ ከኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ወደ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ማደጋቸውን ያረጋገጡት መከላከያዎች በቀጣይ ዓመት የሊጉ ውድድር ተጠናክረው ለመቅረብ በዝውውር ገበያው ላይ እንቅስቃሴ እያደረጉ ይገኛሉ። ከዚህ ቀደም የመሐል ተከላካዩ ልደቱ ጌታቸውን እና የግብ ዘቡ ሙሴ ገብረኪዳንን ዝውውር ሙሉ ለሙሉ ያጠናቀቀው እንዲሁም ኤርሚያስ ኃይሉ፣ ደሳለኝ ደባሽ እና አዲሱ አቱላን የግሉ ለማድረግ የተስማማው ክለቡም ሌላ የአማካይ መስመር ተጫዋች ወደ ስብስቡ መቀላቀሉ ታውቋል።

ክለቡን የተቀላቀለው ተጫዋች ዓለምአንተ ካሳ ነው። የቀድሞ የደደቢት እና ወልዋሎ ዓ/ዩ ተጫዋች የነበረው ዓለምአንተ ያለፉትን ሁለት ዓመታት በመዲናው ክለብ ኢትዮጵያ ቡና ማሳለፉ ይታወቃል። አሁን ደግሞ በጦሩ ቤት የእግርኳስ ህይወቱን ለመቀጠል ፊርማውን ማኖሩ ተረጋግጧል።