ሴቶች ፕሪምየር ሊግ | አርባምንጭ አራት ተጫዋቾች ሲያስፈርም የስድስት ነባሮችን ውል አድሷል

በአንደኛ ዲቪዝዮን የሚሳተፈው አርባምንጭ ከተማ የአራት አዳዲስ ተጫዋቾችን ዝውውር ሲያጠናቅቅ የስድስት ነባር ተጫዋቾችን ውልም አራዝሟል፡፡

በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አንደኛ ዲቪዚዮን የ2013 የውድድር ዘመን ተወዳዳሪ የነበረውና በዓመቱ መጨረሻ ለመውረድ ተገዶ የነበረው አርባምንጭ ከተማ በቅርቡ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የወረዱ ክለቦች በድጋሚ በአንደኛ ዲቪዚዮኑ ይቀጥሉ የሚል መመሪያን በማውጣቱ መነሻነት በፕሪምየር ሊጉ መቀጠሉን አረጋግጧል፡፡ ለቀጣዩ የውድድር ዓመትም ክለቡ አሁን ካለበት በተሻለ መልኩ ለውድድር ለመቅረብ ይረዳው ዘንድ የአዳዲስ ተጫዋቾችን ዝውውር እየፈፀመ የሚገኝ ሲሆን የነባር ተጫዋቾችንም ኮንትራት ለተጨማሪ ዓመት አራዝሟል፡፡

ምህረት ተሰማ ወደ አርባምንጭ ከተማ ማምራቷ ተረጋግጧል፡፡ የቀድሞዋ የጌዲኦ ዲላ ግብ ጠባቂ ያለፉትን ሁለት የውድድር ዓመታት በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ማሳለፏ ይታወሳል፡፡ ሌላኛዋ ፈራሚ በጌዲኦ ዲላ የመሐል ሜዳ ክፍል ጥሩ ግልጋሎት ስትሰጥ የነበረችው ደራ ጎሳ ስትሆን የአማካይ ስፍራ ተጫዋቿ ትውፊት ካዲኖ ከሀዋሳ ከተማ ሦስተኛ ፈራሚ ሆናለች። አራተኛ ፈራሚዋ ደግሞ የተከላካይ ስፍራ ተጫዋች የሆነችው ከአምላክ ከቦሌ ክፍለከተማ ክለቡን ተቀላቅላለች፡፡

ከአዳዲስ ፈራሚዎቹ በተጨማሪ ለምለም አስታጥቄ (ተከላካይ) ፣ ርብቃ ጣሰው (ተከላካይ) ፣ ድርሻዬ መንዛ (ተከላካይ) ፣ ትዝታ ኃይለማርያም (ተከላካይ) ፣ መቅደስ ከበደ (አማካይ) እና ሜሮን ዘሪሁን (አማካይ) ውል ያደሱ ነባር ተጫዋቾች ሆነዋል፡፡