የሀገራችንን የእግርኳስ አስተዳደር ለማዘመን ከሚንቀሳቀሱት ዶ/ር ጋሻው ጋር የተደረገ ቆይታ

👉”ፌዴሬሽኑ ድሮ የነበረው ዓይነት አይደለም ፤ በብዙ ነገሮች ተቀይሯል”

👉”የኢትዮጵያ እግር ኳስ ችግሩ የፋይናንስ ችግር አይደለም። ያለበት ችግር…”

👉”ክለቦች አሁን ማግኘት ከሚችሉት ገንዘብ በላይ ማግኘት ሲችሉ እያገኙ ግን አይደለም”

👉”ክለቦች አሁን ባሉበት አቋም ወደ ዘመነ አስተዳደር ለመምጣት ዝግጁ አይደሉም”

👉”ከፌዴሬሽኑ ጋር በመተባበር በአሜሪካ የሚገኝ ዩኒቨርስቲ በሚያወጣው መስፈርት በየክለቡ ሁለት ሁለት አመራሮች ስልጠና እንዲወስዱ እየሠራን ነው”

ስለኢትዮጵያ እግርኳስ የአስተዳደር ጉዳዮች እንዲያወጉን የጋበዝናቸው ዶ/ር ጋሻው አበዛ በአሁኑ ሰዓት በታውሰን ዩኒቨርስቲ የስፖርት ማኔጅመንት መምህር ሲሆኑ በአሜሪካ በሚገኙ የስፖርት ድርጅቶች ውስጥም በአማካሪነት እየሰሩ ይገኛሉ። በተጓዳኝ ሪሰርቸር (ቃሉ ወደ ተፈጥሯዊ ሳይንስ ቢያመዝንም) የሆኑት ዶ/ር ጋሻው በስፖርት ቢዝነስ ዙሪያ ወደ አራት የሚሆኑ መፅሐፎችን ጽፈዋል።

ከመዲናችን አዲስ አበባ በስተምዕራብ አቅጣጫ በምትገኘው እና ከዋና ከተማው 110 ኪሎ ሜትሮችን ርቃ በምትገኘው ወሊሶ ከተማ የተወለዱት ዶ/ር ጋሻው አብዛኛውን ህይወታቸውን በትምህርት እና ሥራ ከኢትዮጵያ ውጪ እንዳሳለፉ ያወሳሉ። በዚህም ከ12 ዓመታት በፊት ሙሉ ለሙሉ ከሀገር የወጡት ግለሰቡ በሥራ ምክንያት በሴኔጋል ዳካር በተካሄደው እና በ16ኛው የአትሌቲክ ሻምፒዮና ላይ በአፍሪካ አትሌቲክስ ኮንፌደዴሬሽን ውስጥ በማርኬቲንግ አማካሪነት ሰርተዋል። ከዚህ በተጨማሪም በታላቁ ሩጫ በነበራቸው ሚና በቢዝነስ ምክንያት ወደ አውስትራሊያ፣ ባህሬይን፣ ኤምሬትስ፣ እንግሊዝ፣ ስፔን፣ ፈረንሳይ፣ ካናዳ እና የተለያዩ ሀገራት አምርተው ግልጋሎት ሰጥተዋል።

ከወራት በፊት እዚሁ ኢትዮጵያ ውስጥ ከኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን፣ ከኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር እና ከሁለት የሊጉ ክለቦች (ባህር ዳር ከተማ እና ፋሲል ከነማ) ጋር ለመሥራት እንቅስቃሴ የጀመሩት ዶ/ር ጋሻው አበዛ በእግርኳስ አመራር እና አስተዳደር እንዲሁም ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ሰፋ ያለ ቆይታን አድርገዋል።

በአሁኑ ሰዓት በታውሰን ዩኒቨርስቲ የስፖርት ማኔጅመንት መምህር ነዎት። በአሜሪካ ውስጥ በሚገኙ የተለያዩ ድርጅቶች ውስጥም በአማካሪነት ይሠራሉ። በስፖርት ቢዝነስ ዙርያም የተለያዩ መጽሐፍቶችን እንደፃፉ ይታወቃል። ከጠቀስኳቸው ሙያዎች በተጨማሪ በምን አይነት ሠራዎች ላይ አሳልፈዋል?

“የእኔ ጥሩ ጎን ብዬ የማስበው ከውጪው ሳይንስ፣ ትምህርት እና ተሞክሮ በተጨማሪ ኢትዮጵያ ውስጥም ልምድ አለኝ። ወደ ውጪ ከመሄዴ በፊት በታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የመጀመሪያዎቹ አራት እና አምስት ዓመታት ተቋሙ በሁለት እግሩ እንዲቆም እና ራሱን እንዲችል የሠራነው ሥራ አለ። ይህ መሆኑ አሁን ለምሰራው ሥራ እገዛ ይኖረዋል። ጊዜው ራቅ ቢልም በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ላይ ፍንጭ አለኝ። በብዙዎቹ ሀገራት ደግሞ በተለያዩ ድርጅቶች የሰራሁት ሥራ አለ። ለምሳሌ የበረዶ ገና (ice hocky) ኦቱዋ ውስጥ ፣ ዳላስ ውስጥ ያሉ የስፖርት ቡድኖች ጋር በቢዝነስ እና በኦርጋናይዜሽን ስትራክቸር እና በሲስተም ዝርጋታ ዙሪያ ከማስተማር ውጪ ሰርቻለሁ። ነገር ግን የማስተምራቸውም ተማሪዎች ወጥተው የሚሰሩ ናቸው። እንዴት መሥራት እንዳለባቸው ነው የማስተምራቸው።”

እንዳሉኝ በኢትዮጵያ ስፖርት ላይ የመሥራቱ ተሞክሮ አለዎት። እግርኳሱንም በቅርበት ሲከታተሉ እንደነበር አውቃለሁ። በፊት ከሚያውቁት አንፃር አሁን ላይ ያለውን አጠቃላይ የኢትዮጵያን የእግርኳስ ገፅታ እንዴት ይገልፁታል?

“ተስፋ ሰጪ ብዬ እጀምራለሁ ፤ በጣም ተስፋ ሰጪ እና የሚበረታታ ነው። በተለይ ደግሞ ሊጉ ከፌዴሬሽኑ ወጥቶ ራሱን ችሎ መቆሙ እኔ ለምሰራው ሥራ እንደምሳሌ ነው የምጠቅሰው። ሰዎች አሁን ‘በስፖንሰርሺፕ እና በትኬት ሽያጭ ምንድነው የምናደርገው?’ ሲሉ ‘ስለዲኤስ ቲቪ ከሦስት ዓመታት በፊት አስቦት የሚያውቅ ሰው ነበረ ወይ?’ ነው እንደ አንድ ምሳሌ የማደርገው። የቴሌቪዥን ባለቤትነት ሽያጭ መብት ዙሪያ ሊጉ የሰራው ሥራ እጅግ የሚበረታታ ነው። ገንዘብ ደግሞ ብዙ ነገሮችን ይቀርፋል። የሚገኘውም ገቢ ቀላል አይደለም። ፌዴሬሽኑም ድሮ የነበረው ዓይነት አይደለም ፤ በብዙ ነገሮች ተቀይሯል። በእኔ ልምድ ብሩህ የሆኑ ነገሮችን አርቀው የሚያስቡ አመራሮች አሉት ብዬ አስባለሁ። በዚህም በፊት ከነበራው አንፃር አሁን ያለው እግርኳስ ብዙ ማደግ የሚገባው ነገር ቢኖርም አሁን ላይ እየታዩ ካሉት ለውጦች አንፃር ግን አበረታች የሚባል ነው።”

በሥራ ምክንያት ከኢትዮጵያ ውጪ በርካታ ሀገራት የመሔዱን ዕድል አግኝተዋል። ከሌሎች ሀገሮች ጋር ሲተያይ በሀገራችን የክለቦች እና የፌዴሬሽን አስተዳደር ምን ደረጃ ላይ ነው ያለው ማለት እንችላለን?

“በማንኛውም አስተዳደር ውስጥ አራት ሀብቶች አሉ ፤ የቁሳቁስ ፣ የገንዘብ ፣ የመረጃ እና የሰው ኃይል። ከእነዚህ ውስጥ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ችግሩ የፋይናንስ ችግር አይደለም። ያለበት ችግር የፋይናንስ አስተዳደር ችግር ነው። መፈታትም ያለበትም ይህ ነው። ፋይናንስን ስታስተዳድር ገቢን ማሳደግ ብቻ አይደለም ወጪንም መቀነስ ነው። ጥቅም ላይ የሚውለው ገንዘብ ይቁም ማለትም አይደለም። ምክንያታዊ መሆን እና ለሚወጣው ገንዘብ ምላሽ የሚገኝ መሆኑን ማወቅ ነው። ከዚህ አንፃር በፋይናንስ ዙሪያ ሊፈቱ የሚገቡ ብዙ ጉዳዮች አሉ። በሌሎቹ ሦስት ሀብቶችም እንዲሁም መጎልበት ያሉባቸው ነገሮች አሉ።”

እግርኳሳችን ውስጥ ያለው የአስተዳደር መዋዠቅ መንስዔ ምንድነው ብለው ያስባሉ? ሰውስ አጥተን ነው ብለው ያምናሉ?
“ለእኔ ሁለቱም ነው። ሰውም አለን ሰውም አጥተናል። በእውነቱ በፌዴሬሽንም፣ በክለቦችም ፣ በሊጉም ደረጃ አሁን እየሰሩ ያሉትን ሰዎች ላመሰግን እወዳለሁ ፤ ለውጥ አምጥተዋል ፣ ለውጥ አሳይተውናል ፤ አያውቁም ማለትም ይከብዳል። ነገር ግን ደግሞ እነሱ ዕውቀት ባለው ሰው መታገዝ አለባቸው። እናም ለዚህ ጥያቄ መልስ የሚሆነው የተማረ ፣ የሰለጠነ ሳይንሱን የሚያውቅ የሌሎችን ተሞክሮ እና ስኬታማ አካሄድ ያነበበ እና የተገነዘበ የሰው ኃይል የግድ ይላል። የመጨረሻው መፍትሄ መስሎም የሚሰማኝ በእግርኳስ አስተዳደር እና ገበያ የሰለጠነ ሰው እገዛ የግድ እንደሚል ነው።”

ወደ ክለቦች አስተዳደር ስንመጣ አሁን ላይ ወደ ሕዝባዊነት ለመምጣት ጥረት ሲያደርጉ ይታያል። ክለቦችን ሕዝባዊ ማድረግ በትክክል ምን ማለት ነው? የሚያስገኘው ጥቅምስ ምንድን ነው?

“በቅድሚያ ሕዝባዊ ከመሆን በፊት ሊሰሩ የሚገባቸው ብዙ ስራዎች እንዳሉ መጠቆም እፈልጋለሁ። የገቢ ምንጭን ማጎልበት ፣ ሰውን ማሰልጠን ፣ ማሰልጠን ብቻ ሳይሆን መፈፀም ተፈፅሞም መሬት ላይ ሲወርድ የሚገጥሙ ዕንቅፋቶችን መቅረፍ መቻል አለብን። ክለቦች አሁን ማግኘት ከሚችሉት ገንዘብ በላይ ማግኘት ሲችሉ እያገኙ አይደለም። ብዙ መሸጥ የሚችሉ ዕድሎች እየተሸጡ አይደሉም። ለምሳሌ ከስፖንሰርሺፕ አራት ደረጃዎች አንፃር የመጀመሪያው የሆነው ትኩረትን የመሳብ ሂደት እንኳን በአግባቡ አይከወንም። በግለሰብ ደረጃ ሊሰራ የሚችል ባነር የመስቀል ዓይነት ስራዎች እንካን እየተሰሩ አይደለም። በዛ ደረጃ ነው። እሱን እሱን ከሰራን በኋላ ነው ክለቦችን ህዝባዊ ወደማድረጉ ልንሄድ የምንችለው። ይህንን ብለን ወደ ጥያቄው ስንመለስ የክለቦች ሕዝባዊነት እና የባለቤትነት ይዞታ ከሀገር ሀገር ይለያያል። በአውሮፓ ትልልቅ ከሚባሉት ውስጥ የእንግሊዝ ፣ የጀርመን ፣ የጣሊያን እና የስፔን እንኳን የተለያየ ነው። እንግሊዝ ውስጥ እንኳን የተለያየ ነው። የውጪ ባለሀብቶች የያዟቸው አሉ ፣ የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች የያዟቸው ወደ ስምንት የሚደርሱ አሉ። በአህጉራችንም ካጠናሁዋቸው ውስጥ የግብፅ ከደቡብ አፍሪካ የተለየ ነው። ወደ ምዕራብ ሄደህ የናይጄሪያን ብታይ በምስራቅ ካለው ከኬኒያ የተለየ ነው። ስለዚህ የሌሎቹን ልምድ አምጥተህ ኢትዮጵያ ውስጥ አታስቀምጠውም። እስካሀን ማነው በባለቤትነት የቆየው? ነባራዊ ሁኔታው ምን ይመስላል? የሚሉትን ነገሮች ማጥናት ያስፈልጋል። በዚህ ረገድ የእኛ ጥናት እንደተመለከተው ለኢትዮጵያ ሀገር በቀል የባለቤትነት ይዞታ ያስፈልጋታል። ያ ማለት ሦስት ዋና ባለድርሻዎች አሉን። ቅድም ያልኳቸውን የገቢ ምንጩን ፣ ድርጅታዊ መዋቅሩን እና የሰው ኃይል ስልጠናውን ከሰራን በኋላ ክለቦችን ወደ ሕዝባዊነት ስናመጣ ሦስት ባለቤትነት ሊኖራቸው የሚችላቸውን አካላት እናስባለን። አንደኛ መንግስት ፣ ባለሀብቶች እና ደጋፊዎች። ክፍፍሉ ለሕዝብ ግብዓት የተደመደመ ባይሆንም ለምሳሌ 30 30 40 ሊሆን ይችላል። ለምሳሌ ነው ያልኩት ይህ ለፋሲል ከሰራ ለባህር ዳር ላይሰራ ይችላል። እሱን ከክለቦቹ ጋር መወያየት ይጠይቃል። ሊጉም ደግሞ ማዕቀፍ ያወጣል። ማን ባለቤት ይሁን ማን አይሁን የሚለውን ሊጉ ነው የሚወስነው። ጥያቄህን ለመመለስ መንግሥት ባለድርሻ ይሆናል የሚወጣው ግን ቀስ እያለ ድጎማውን እየቀነሰ ነው። እንግዲህ ይህንን የምናደርገው የራሱን የገቢ ኃይል አመንጭቶ ወጪውን መሸፈን የሚችልበት ደረጃ ላይ ሲደርስ ነው። የባለሀብቶችን ቆየት ብዬ ላብራራ እና ወደ ደጋፊዎች ልምጣ። ደጋፊዎች ስንል የተመዘገቡ ደጋፊዎችን ነው። ለምሳሌ ተመዝግበው ለአምስት ዓመታት የቆዩ ደጋፊዎች ሕዝባዊ ሲሆን የባለቤትነት ድርሻ የመግባት ዕድል ይኖራቸዋል። ባለሀብቶች ጋር ስንመጣ አንደኛ የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ፣ ሁለተኛ የንግድ ድርጅቶች (በአካባቢው ያሉ ድርጅቶች እና ተቋሞች)፣ ሦስተኛ ነዋሪው ህዝብ (ደጋፊ ሆኖ ካልተመዘገበ እንደባለሀብት ስለሚቆጠር) ሌላው ዲያስፖራውን (የአካባቢው ተወላጅ ሆኖ በውጪ ሀገር የሚኖር) ያካትታል። በሂደት ግን የውጪ ባለሀብቶችንም ልንጋብዝ እንችላለን። እና ባለሀብት የሚለው ሰፊ ሆኖ የሦስቱ የመንግስት ፣ የባለሀብት እና የደጋፊዎች ባለቤትነት የሚይዘው በኢትዮጵያ ልክ የተሰፋ የባለቤትነት ቀመር ነው ብለን ነው የምናስበው።”

እርስዎ ባደረጓቸው ጥናቶች የኢትዮጵያ ክለቦች ወደዚህ የዘመነ መንገድ ለመግባት ዝግጁ ናቸው ብለው ያስባሉ?

“አሁን ባሉበት አቋም ዝግጁ አይደሉም። ግን ወደዛ የሚወስዳቸውን መንገድ ነው እየዘረጋን ያለነው። አሁን ከእኛ ጋር ስምምነት የፈረሙት ፋሲል ከነማ እና ባህር ዳር ከተማ ናቸው። የእናንተ አንባቢያንም ማወቅ ያለባቸው ዕድሉ ለሁሉም ክለቦች ክፍት መሆኑን ነው። ሁለቱ ክለቦች የተለየ ጉጉት አሳይተው በመምጣት አብረው ለመስራት በማሰባቸው ከእነሱ ጋር መስራት ጀምረናል። እነሱ ሞዴል ሆነው ያገለግላሉ ብለን እናስባለን። ከሌሎችም ክለቦች ጋር በሂደት እንሰራለን። የምንሰራው የገቢ ምንጫቸውን ማጎልበት ላይ ነው። አሁን ለምሳሌ ስፖንሰርሺፕ አሁንም ልግስና ነው። አንድ ተቋም ስፖንሰር ሲያደርግ በምላሹ ሊያገኝ የሚገባው ነገር አለ። ለምሳሌ አስር ሚሊየን ከሰጠህ አንድ እንኳን ሰራተኛ ቀጥረሀል ወይ ያንን ለስፖንሰሩ ምላሽ የሚሰጥ እና የሚያስተዳድር? በዓመት ሁለት መቶ ሺህ የምትከፍለው ሊሆን ይችላል። ይህ እየሆነ ያለ አይመስለኝም። ለምሳሌ ስፖንሰርሺፕ ምን ማለት ነው? እንዴት ነው የምትፈልገው? ፕሮፖዛል እንዴት ነው የምታዘጋጀው? ምን ምን ጥቅም ነው የምታቀርበው? የስፖንሰርሺፑስ ዓላማ ምንድነው? አንድ ድርጅት እኮ ስፖንሰር ሲያደርግ ዓላማው ደጋፊዎቹ ጋር ለመድረስ ነው። ደጋፊዎቹ የእሱን ምርት እና አገልግሎት እንዲገዙ ነው። ከስፖንሰርሺፕ ሌላ ደግሞ ትኬት ሽያጭ። ትኬት ሽያጫችን እጅግ እጅግ ወደ ኋላ የቀረ ነው። አሜሪካ የዛሬ መቶ ሀያ ምናምን ዓመት ቤዝ ቦል ሲጀመር የነበረው ዓይነት ነው አሁንም ያለው። እሱን ባህል መቀየር መቻል አለብን። መሰረተ ልማቱን አስተካክሎ እያንዳንዱ ክለብ ስፖንሰር ከሆነው ባንክ ጋር ተስማምቶ በመስራት ወደ መሬት መውረድ መቻል አለበት። ሦስተኛ የንግድ ምልክትን ያያዙ ቁሳቁሶችን የተመለከተ ነው። ስካርቭ እና ቲሸርቶችን ብቻ ነው የምናወቀው። ነገር ግን ብዙ ሌሎች ምርቶች አሉ። ለምሳሌ የማንቸስተር ሲቲ ሻይ ሁሉ አለ። ለምን የፋሲል ከነማ ሻይ አንሸጥም? በውጪው ዓለም ይህ የሚደረገው ከሌሎች አምራች ድርጅቶች ጋር አብሮ በመስራት ነው። እያንዳንዱን የምርት ዓይነት ለተለያዩ አምራቾች በመስጠት ነው የሚሰራው። እሱን ባህል ማዳበር የውጪዎቹን ተሞክሮ በማምጣት ከሳይንሱ ጋር በማጣጣም እና ከንባራዊው ሁኔታ ጋር በታረቀ መልኩ ነው ለመስራት ያሰብነው። ሌላው ደግሞ የስያሜ መብት ነው። ክለቦች የመወዳደሪያ ስፍራ ኖሯቸው ስያሜውን ለድርጅቶች በመስጠት ገንዘብ እንዲሰሩ ማድሩግ ይቻላል። የስታድየም ውስጥ አገልግሎቶች ፣ የሀገር ውስጥ የሚዲያ መብት (የዲኤስቲቪ የውጪ ነው) ብዙ ብዙ ገንዘብ ማግኛ የሆኑ ነገሮች ላይ እየሰራን አይደለም። እነዚህ ላይ ለመስራት ግን በቅድሚያ ሲስተም ላይ መስራት ይጠይቃል። የሚሰራበት መንገድ ከተቀየሰ በኋላ ደግሞ ሰው እናሰባጥራለን። ለምሳሌ የዩኒቨርሲቲ የመጨረሻ ተማሪዎችን በማሳታፍ ስኬታማ ከሆኑ በቀጣይ ተቀጣሪ እንዲሆኑ በማድረግ እንዲሁም ከደጋፊዎች ውስጥም ኢንጂነሮች ፣ ዶክተሮች እና የብዙ ሙያ ባለቤቶች ሊኖሩ ይችላሉ። ፍላጎቱ ካላቸው የሚመጣው ሲስተም አካል ሆነው ሊቀጥሉ ይችላሉ። ክለቡን መቀየርን የሚያውቁ ሰዎች ወደ ክለቡ መቀየር ሚና ውስጥ ይገባሉ ማለት ነው። ያንን መሬት ላይ አውርደን ክትትል እናደርጋለን። ያ ነገር ስኬታማ ሲሆን እና ወጪን ቀንሶ ምክንያታዊ በሆነ ሁኔታ ብቻ ሲወጣ እና ገቢ ሲጎለብት የፋይናንስ ዐቅም ይጎለብታል። ያኔ ክለቡ ራሱን ይችላል። ይህ እንደሚሆን ደግሞ አልጠራጠርም። ያኔ ነው ወደ ህዝባዊነት መሄድ የሚቻለው። ጥያቄው ረጅም መልስ የሚያስፈልገው ስለሆነ ነው። አሁን ባሉባት አቋም አይችሉም ግን ደግሞ እንዲችሉ ነው እየሰራን ያለነው”

በተለምዶው በእግር ኳሳችን ከታች ጀምሮ ቴክኒኩ ላይ መስራት ነው የሚኖርብን ፤ አይ ከላይ አስተዳደሩ ላይ ብንሰራ ነው ለውጥ የሚጣው የሚሉ ሁለት ሀሳቦች አሉ። እርሶ ለየትኛው ቅድሚያ መሰጠት አለበት ይላሉ?

“የእኔ ጥያቄ ለምን ሁለቱ በአማራጭነት ቀረቡ? የሚል ነው። ለምን ሁለቱም አብሩው አይጀመሩም? በሁለቱም አቅጣጫዎች መስራት ይቻላል። የታዳጊዎች ሥልጠና እና ልማት ላይ እየተሰራ ከላይ አስተዳደራዊ ለውጥ ለማድረግ የማይቻልበት ምክንያት አይታየኝም። ሁለቱ የሚጣረሱም አይደሉም። አንዱ ስለተደረገ ሌላው የሚፈርስበት ሁኔታም የለም። ምናአልባት አስተዳደራዊ መዋቅሩ እየበረታ ስላልሆነ ታዳጊዎች ልማትን ላያፈናፍነው ይችል ይሆናል። ግን ሁለቱም አብረው የማይሰሩበት ሁኔታ አይታየኝም። ነገሮችን ነጭ እና ጥቁር አድርጎ ማየት አይገባም። ሐምራዊ፣ ቢጫ ፣ አረንጓዴ፣ ሰማያዊ አለ አይደል መሀል ላይ? እና አንዱ ካለ ሌላው አይኖርም ማለት አይደለም ፤ ሁለቱንም ማድረግ ይቻላል። ውይይቱ ሊሆን የሚገባው እንዴት ነው ማድረግ የሚቻለው ? የሚለው ላይ ነው።”

አሁን ክለቦቻችን ካሉበት ደረጃ ሲታይ የራሳቸውን ገቢ ማመንጨት ችለው አሁን ወዳሉት ደረጃ ለመድረስ በአማካይ ምን ያህል ጊዜ ሊወስድባቸው ይችላል?

“የምናወራው በጣም ዘላቂ ስለሆነ ነገር ነው። ሲስተም ሲዘረጋ ዕድሜ ልክ በለው ፤ እየተሻሻለ የሚሄድ ስለሆነ። እንደየክለቦቹ አመራር አካላት ፍላጎት እና የመተግበር ተነሳሽነት ይወሰናል። ነገር ግን እኛ አሁን ከክለቦቹ ጋር የፈፀምነው ስምምነት ከአስር ወር ባላነሰ ጊዜ ውስጥ ነው ወደ መሬት የምናወርደው። በአስር ወር ውስጥ ብዙ ነገር ይሰራል ፤ የፕሮጀክት አስተዳደር ጉዳይ ነው። በዚህ ጊዜ ውስጥ መሬት አውርደን ሰው አሰልጥነን ለክለቡ አስረክበን ያሰለጠናቸው ሰዎች መተግበር ሲጀምሩ እየተከታተልን የሚያጋጥማቸውን ነገሮች እየፈታን ነው የምንሄደው። ስለዚህ ቢያንስ ከሁለት ዓመት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ ነው ተስፋ የማደርገው። የሌሎች ሰዎች እገዛ ካለበት በሁለት ዓመት ውስጥ ከደረስን ጥሩ ነው። በሦስት ዓመት ውስጥም ከደረስን መልካም ነው። በጊዜ መገደብ አልችልም። የሌሌች አጋር አካላት የሁኔታ እና እገዛ ግን ይፈልጋል።”

በጠቀሱልኝ ጊዜያት ውስጥ በቅደም ተከተል የሚሰሩ ስራዎችን በዝርዝር አስረዱን እስቲ?

“በመጀመሪያ የምንሰራው የመዋቅር ዝርጋታ ነው። የውስጣዊ እና ውጪያዊ ድርጅታዊ መዋቅር ምን ይመስላል ? ምን መልክ አለው ? የሚያሰራ ነው ወይ ? ምን እንጨምርበት ? ቅድም እንዳልኩት ያልደፈረሰውን አታጠራም የደፈረሰውን ነው የምታፀዳው። መልካም የሆነውን ታቆየዋለህ። መቼም የሚጨመር ነገር እንዳለ ያለው ውጤት የሚናገረው ነው። ባለው ላይ ጨምረን አስተካክለን እያንዳንዱ ድርጅት ውስጥ የሚገቡ ሰራተኞች ወይም አባላት ምን ሚና አላቸው ? የተቆጠረ እና የተመዘነ መሆን አለበት። ምክንያቱም አንድ ሰራተኛ ስትቀጥር በየወሩ በየስድስት ወሩ በበየዓመቱ መመዝን መቻል አለብህ። ዓመቱ መጨረሻ ላይ የዛ ሰው ብቃት የሚለካበት መመዘኛ መኖር አለበት። ከዚህ አንፃር መዋቅሩ ከተሰራ በኋላ ሰዎችን ነው የምንመለምለው። የሚዘረጋው መዋቅር የራሱ የመተግበሪያ ሰነድ ይኖረዋል። ለምሳሌ የስፖንሰርሺፕ ፣ የትኬት ሽያጭ ፣ የስታዲየም ውስጥ አገልግሎት ፣ የስታዲያም እና መለማመጃ ቦታዎች መጠሪያ ሁሉ የመተገበሪያ ሰነዶች ይኖሯቸዋል። ይህን ተከትሎ ይህንን የሚተገብሩ ሰዎች ሥልጠና እናሰለጥናለን። የሰለጠኑት ሰዎች ወደ መሬት እንዲያወርዱት ማድረግ እና መከታተል ነው የእኛ ሥራ። የእኛ ተስፋ በአግባቡ የሰለጠነ ሰው የታቀደውን ነገር ያደርገዋል የሚል ነው። ከዛ በኋላ ነው ወደ ማህበረሰብ ባለቤትነት ይዞታ ክለቦች እንዲሸጋገሩ የምናስበው።”

ይህንን ሥራ መቼ ነበር የጠነሰሱት?

“ብዙዎቹ ዛሬ የምሰራቸው ነገሮች ከዛሬ አምስት እና ስድስት ዓመታት በፊት የታቀዱ ናቸው። ዛሬ ላይ ተፈፃሚ ይሁን እንጂ ብዙ ታሽተው እና ታይተው ካልሆነ በቀር መሬት ላይ ስታወርዳቸው እንደኳስ ነጥረው የሚቀሩ አይደሉም። እንደ አሎሎ እዛው እንዲሰክኑ ብዙ የሚሰሩ ጥርጊያ መንገዶች አሉ። ጥርጊያ መንገዶቹ አንድ አምስት ዓመት ፈጅተው ነው እዚህ ላይ የደረስነው።”

ከወራት በፊት ለኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ክለቦች የሰጡት ሥልጠና ነበር። ስለ ሥልጠናው እና ውጤቱ እንዲሁም ከሊጉ አክሲዮን ማኅበር ጋር ስለጀመሩት የሥራ ግንኙነት አውጉኝ?

“አዎ በፌዴሬሽኑ ፕሬዘዳንት ግብዣ ታህሳስ ላይ መጥቼ ሥልጠና ሰጥቼ ነበር። ያ ሥልጠና ነው ዛሬ ላለንበት ደረጃ ያደረሰን። ሥልጠናው ግንዛቤ ማስጨባጫ ነበር። ያልነበረ ነገር ስታመጣ ለሰዎች የማስረዳት ግዴታው ያንተ ነው። ያ በመሆኑም እና ግንዛቤው በመፈጠሩ ነው አሁን ላይ የደረስነው። ስልጠናው ፍሬ አፍርቷል ማለት ነው። ጅማሯችንን በማየትም ሌሎች ክለቦች እንደሚቀላቀሉን ተስፋ አድርጋለሁ። በዚህ ረገድ የፌዴሬሽኑን ፕሬዘዳንት እና ፌዴሬሽኑን ላመሰግን እወዳለሁ ፤ በሥልጠና በጣም ያምናሉ። አንድ እዚህ ጋር መጠቆም የምፈልገው ነገር ፌዴሬሽኑ በአሜሪካ ካለ ዩኒቨርስቲ ጋር በመሆን ከእያንዳንዱ ክለብ ሁለት ሁለት ሰው የሚወከልበት የዲፕሎማ ሰርተፍኬት ፕሮግራም እያዘጋጀ ነው። በኮቪድ ምክንያት ነው የተጓተተው። ከእያንዳንዱ ክለብ ሁለት ሁለት አመራሮች ተመርጠው ከአራት ወራት እስከ አምስት ወራት የሚፈጅ ትምህርት በሀብት አስተዳደር ማለትም የቁሳቁስ ፣ የገንዘብ ፣ የሰው ኃይል እና የመረጃ አስተዳደር እንዲሁም በፋይናንስ አስተዳደር ላይ ሥልጠና ይወስዳሉ። እስካሁን የተጓተተውም የትምህርት አጠጣጡ ህጋዊ ዕውቅና እስኪሰጠው ድረስ ነው። የፌዴሬሽኑን ፕሬዘዳንት ላላቸው ተነሳሽነት በዚህ ረገድ ማመስገን እፈልጋለሁ። ከሊጉ ጋር ደግሞ ከላይ ካለው አመራሩ ጀምሮ እስከስር የክለብ አደረጃጀት ፣ አሰራር እና አመራር ድረስ እንዲፈተሽ ይፈለጋል። ጥናት ላይ የተመሰረተ የመፍትሄ ሀሳብ ነው የምናቀርበው ፤ ከማስፈፀሚያው ማዕቀፍ ጋር። በዚህ ዙሪያ የአምስት ወር ገደብ ያለው በጣም ሰፊ እና ጥልቅ የሆነ ጥናት ብዙ ድርሻ ያላቸው አካላትን የሚያካትት ዳኞችን ፣ አሰልጣኞችን ፣ ደጋፊዎችን ፣ የህክምና ባለሙያዎችን ፣ ኤጀንቶችን የክለብ አመራሮችን ፣ የሊጉን አመራሮችን ፣ የሊጉን ሰራተኞችን ፣ የፌዴሬሽኑን አመራሮች እና ሰራተኞች ሀሳብ የሚሰበስብ ሊጉን የሚያደረጅ ከፌዴሬሽኑ ጋር ያለውን አንድነት እና ልዩነት የሚለይ እና የዘመነ የሚያደርገውን የመፍትሄ ሀሳብ ለማቅረብ ነው እየሰራን ያለነው። ይህ ወደ ሁለተኛው ወር እየሄደ ነው ሦስት ወር ነው የሚቀረው።”

ከፌዴሬሽኑ ጋር በመሥራት ላይ ያላችሁት ነገር እምብዛም አልተሰማም ስለሱ ተጨማሪ ማብራሪያ ቢሰጡኝ?

“አዎ ብዙ ይፋ አላደረግነውም እንጂ እኔ የማስተምርበት አሜሪካ የሚገኘው ታውሰን ዩንቨርስቲ ከኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ጋር በመተባበር ዩኒቨርስቲው በሚያወጣው መስፈርት በየክለቡ ሁለት ሁለት አመራር ላይ ያሉ ሰዎች ተመርጠው በሀብት አስተዳደር እና በፋይናንስ አስተዳደር ዙሪያ ስልጠና ያገኛሉ። አሁን የምንሰራውን ስራ የሚያግዝ ነው የሚሆነው። ለምሳሌ ስለትኬት ሽያጭ ስታስረዳ ከዜሮ ተነስተህ አይሆንም። የተረዳ እና የሚያውቅ ሰው ጋር ነው የምታወራው። ስለዚህ በኋላ ላይ ካሰለጠንናቸው ሰዎች ጋር የሰለጠነ የክለብ አመራር የተሻለ ደረጃ ላይ ያደርሰዋል ብለን ነው የምናስበው። ከሦስቱም አካላት ጋር ግንኙነት በማድረግ የተሻለ ነገር ለመስራት እየሞከርን ነው።”

ይህ እንቅስቃሴ አሁን ምን ደረጃ ላይ ነው?

“አሁን ላይ ኮቪድ አጓቶታል። አሜሪካ ውስጥ የመንግስት ዩኒቨርሲቲ ከሆነ ለምሳሌ ለአዳማ ዩኒቨርሲቲ ለሚሰጠው ለየት ያለ የሰርተፍኬት ዲፕሎማ የኦሮሚያ ትምህርት ቢሮ ማፅደቅ ይኖርበታል። እሱ አሰራር ላይ ነው ኮቪድ እክል የፈጠረው። ከዛ ወደታች ወርዶ ሲያልቅ ግን ሥልጠናው ወዲያው ይጀምራል።”

ስለዚህ አሁን ላይ የሚሰሯቸው ሥራዎች ምንድን ናቸው?

“ስለዚህ በአጠቃላይ አሁን ላይ ከሊጉ ፣ ከክለቦች እና ከፌዴሬሽን ጋር እየሰራን ነው። ከዚህ ውጪ አስተምራለሁ። አራት መፅሀፎች አሉኝ። ሁለቱ አሁን ላይ ይወጣሉ። አንዱ እንደውም ሐምሌ ላይ ወጥቷል። በምርምር ሥራዬ እቀጥላለሁ። እዚህ ኢትዮጵያ ውስጥም አብረውኝ የሚሰሩ ጎበዝ ጎበዝ ኢትዮጵያዊያን አሉ። እነሱን በማሰልጠን እና በማብቃት ነገ የራሳቸውን የስፖርት አማካሪ ድርጅት እንዲፈጥሩ ብዬ አስባለሁ።”

ስለግል ህይወትዎ ደግሞ እናውራ። ትውልድ እና እድገቶ እንዲሁም የትምህርት ጊዜዎ አጫውቱኝ እስቲ?

“ትውልዴ ወሊሶ ነው። አብዛኛውን ህይወቴን ያሳለፍኩት አዲስ አበባ ላይ ነው። የህይወቴን 1/3ኛ የሚሆነውን ደግሞ በትምህርትም በሥራም ከኢትዮጵያ ውጪ ነው ያሳለፍኩት። ጠቅልዬ ከሀገር ቤት ከወጣው ወደ 12 ዓመት ይሆነኛል። በሥራ ምክንያት በሴኔጋል ዳካር በተካሄደው እና በ16ኛው የአትሌቲክ ሻምፒዮና ላይ በአፍሪካ አትሌቲክስ ኮንፌደዴሬሽን ውስጥ በማርኬቲንግ አማካሪነት ሰርቻለው። ከዚህ በተጨማሪም በታላቁ ሩጫ በነበረኝ ሚና በቢዝነስ ምክንያት ወደ አውስትራሊያ፣ ባህሬን፣ ኤምሬትስ፣ እንግሊዝ፣ ስፔን፣ ፈረንሳይ፣ ካናዳ አምርቼ ልምድ አግኝቻለሁ።”

የቤተሰብ ህይወትዎስ ምን ይመስላል?

“ቤተሰብ አለኝ። የምወዳት ባለቤቴ አለች ፣ ልጄም አለ። አብረን ነው የምንኖረው። አብረንም ነው እየዞርን ያለነው።”

ከባህር ዳር ከተማ እና ፋሲል ከነማ ጋር አብሮ ለመሥራት ስምምነት ፈፅማችኋል። ሌሎች ክለቦች ከእርሶው ጋር አብሮ ለመስራት ቢፈልጉ በምን መንገድ ሊያገኝዎት ይችላሉ ?

“በእናንተ በሶከር ኢትዮጵያ በኩል ፣ በሊጉ በኩልም ሊያገኙኝ ይችላሉ። አስፈላጊ ከሆነ ደግሞ ታውሰን ዩኒቨርስቲን ጉግል ቢያደርጉ ኢ-ሜሌንም ሆነ ስልኬን እዛ ላይ ሊያገኙ ይችላሉ።”

ቀረ የሚሉት ሀሳብ ካለ ልቀበሎት እና ቆይታችንን እናገባድ…?

“አሁን ስላገኘሁት አይደለም፤ ነገር ግን ሶከር ኢትዮጵያን ማመስገን እፈልጋለሁ። ለእኔ ስለኢትዮጵያ እግር ኳስ መረጃ በምፈልግበት ጊዜ ዋነኛ ምንአልባትም ብቸኛ የመረጃ ምንጭ ሆኖ ነው የሚያገለግለኝ እና በዚህ ዙሪያ እጅጉን ላመሰግናቸሁ እወዳለሁ። አደራ በርቱ ቀጥሉበት እላለሁ። የተለያዩ አካላትም ሊያግዛችሁ ስለሚገባ ድጋፍ እንዲያደርጉላችሁ ጭምር አደራ እላለሁ።”