ቅዱስ ጊዮርጊሶች አዲስ አንበሎችን መርጠዋል

ቡድኑን በአምበልነት ሲመሩ የነበሩት ተጫዋቾች ከክለቡ በመለያየታቸው ምክንያት ቅዱስ ጊዮርጊስ አዲስ አንበሎችን መምረጡ ታውቋል።

ለ2014 የውድድር ዘመን አዲስ አሰልጣኝ የሾመው ቅዱስ ጊዮርጊሶች በትናንትናው ዕለት ቢሸፍቱ በሚገኘው የክቡር ይድነቃቸው አካዳሚ ለቅድመ ዝግጅት ከተሰባሰቡ በኃላ የክለቡ የቦርድ አመራሮች የቡድኑ አባላት እና አዲሱ አሰልጣኝ ዝላትኮ ክራምፓቲች በተገኙበት በይፋ ትውውቅ እና ምክክር አድርገዋል። በዚሁ ዕለት ከትውውቁ ባሻገር በቀጣይ ዓመት ቡድኑን በአንበልነት የሚመሩ ሁለቱ ተጫዋቾች እነማን እንደሆኑ ታውቋል።

ያለፉትን ሰባት ዓመታት ከታዳጊ ቡድን አንስቶ እስከ ዋናው ቡድን ድረስ ፈረሰኞቹን እያገለገለ የሚገኘው ናትናኤል ዘለቀ ቀዳሚ አንበል ሆኖ ሲመረጥ ከመድን ቅዱስ ጊዮርጊስን ከተቀላቀለ በኋላ በተመሳሳይ ለሰባት ዓመታት ቡድኑን ያገለገለው ሳላዲን በርጌቾ ሁለተኛ አንበል ሆኖ ተሹሟል። ሦስተኛ አንበል የሚሆነው በቅርቡ የሚታወቅ መሆኑን ለማወቅም ችለናል።

ከዚህ ቀደም ጌታነህ ከበደ፣ ምንተስኖት አዳነ፣ ሳላዲን ሰዒድ እና አስቻለው ታመነ ፈረሰኞቹን በአንበልነት ሲመሩ እንደነበር ይታወቃል። አዲሶቹ አምበሎች ሳላዲን በርጌቾ እና ናትናኤል ዘለቀም አልፎ አልፎ አንበል በመሆን ቡድኑን የመሩበት አጋጣሚ ነበር።