የዋልያዎቹ ዋና አሠልጣኝ ነገ ማለዳ ጉዞ ያደርጋሉ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዋና አሠልጣኝ ውበቱ አባተ ነገ ማለዳ ከሀገር ውጪ ጉዞ እንደሚያደርጉ ታውቋል።

ለኳታሩ የዓለም ዋንጫ ለመብቃት ከፊቱ የምድብ የማጣሪያ ጨዋታዎች የሚጠብቁት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በአዳማ መቀመጫውን በማድረግ ዝግጅት እያደረገ እንደሆነ ይታወቃል። የብሔራዊ ቡድኑ አሠልጣኝ ውበቱ አባተም ቡድኑን በቀን ሁለት ጊዜ እያዘጋጁት የሚገኝ ቢሆንም ነገ ማለዳ ግን ወደ ካሜሩን እንደሚያመሩ ሶከር ኢትዮጵያ ተረድታለች።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከስምንት ዓመታት በኋላ ወደ አፍሪካ ዋንጫው እንዳለፈ ይታወሳል። የዚህ ውድድር የምድብ ድልድልም በነገው ዕለት በካሜሩን ያውንዴ ሴንተር እንደሚወጣ ከቀናት በፊት ገልፀን ነበር። የእጣ ማውጣት ሥነ-ስርዓቱን ለመከታተል የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳይያስ ጂራ እና የጽሕፈት ቤት ኃላፊው አቶ ባህሩ ጥላሁን ወደ ስፍራው እንዳመሩ ከደቂቃዎች በፊት የዘገብን ሲሆን አሁን ደግሞ የብሔራዊ ቡድኑ ዋና አሠልጣኝም የአህጉሩ ትልቁ ውድድር የምድብ ድልድል ለመታዘብ ወደ ምዕራብ አፍሪካዊቷ ሀገር (ካሜሩን) እንደሚያመሩ አውቀናል። ሶከር ኢትዮጵያ እንዳረጋገጠችው ከሆነ እስከ አመሻሽ ድረስ ከቡድኑ ጋር አዳማ የነበሩት አሠልጣኙም ነገ በጠዋት ወደ ስፍራው የሚያቀኑ ይሆናል።