ዋልያው በአዳማ ከተማ የሚያደርገውን ዝግጅት እንደቀጠለ ነው

በቀን ሁለት ጊዜ ዝግጅታቸውን እያደረጉ የሚገኙት ዋልያዎቹ ዛሬም መደበኛ ልምምዳቸውን ሲሰሩ ተመልክተናል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ነሐሴ ወር መጨረሻ ላይ ለሚያከናውናቸው ሁለት የዓለም ዋንጫ ማጣርያ ጨዋታዎች መቀመጫውን ከአዲስ አበባ 90 ኪሎ ሜትር ዕርቃ በምትገኘው አዳማ ከተማ በማድረግ ዝግጅት ከጀመረ ቀናቶች ተቆጥረዋል።

ዛሬ ከ10:00 ጀምሮ በአበበ ቢቂላ ስታዲየም የቡድኑ አባላት በተሟላ ሁኔታ ተሰባስበው ልምምዳቸውን ሲከውኑ ተመልከተናል። በማለዳው በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩንቨርስቲ ሜዳ ከሠሩት የቀጠለው ይህ ሁለተኛው ጠንከር ያለ ልምምዳቸው ነው።

ከአንድ ሰዓት ተኩል በላይ በቆየው የቡድኑ አመሻሽ ዝግጅት ከኳስ ጋር የተገናኘ የኳስ ቅብብሎች፣ መሐል ባልገባዎች እና ወደ መጨረሻው ደግሞ በፈጣን የማጥቃት እንቅስቃሴ ውስጥ ወደ መከላከል የሚደረግ ሽግግር ላይ ያተኮረ ልምምድ ሲሰሩ ለማየት ችለናል። አሰልጣኝ ውበቱ የሚፈልጉትን ታክቲክ ልጆቻቸው እንዲተገብሩ ለማድረግ በተደጋጋሚ የጨዋታውን እንቅስቃሴ በማቋረጥ ያስረዱ እንደነበረ ታዝበናል።

ከቡድን ዜና ጋር በተያያዘ በትናንትናው የብሔራዊ ቡድን ዝግጅት ባቀረብነው ዘገባ አስቻለው ታመነ፣ አቡበከር ናስር እና ሱራፌል ዳኛቸው ቀለል ያለ ጉዳት እንዳጋጠማቸው መግለፃችን ይታወቃል። በዛሬው ዕለትም ሦስቱም የቡድኑ የልምምድ አካል በመሆን የተለያዩ ተግባሮችን ሲከውኑ አይተናል።

የዋልያዎቹ የኋላ ደጀን አስቻለው ታመነ ከቡድኑ ተነጥሎ ብቻውን ሙሉ የሜዳውን ክፍል የመሮጥ እና በህክምናው ባለሙያ የሚሰጠውን የልምምድ ተግባራት ሲከውን ቆይቶ በኃላ ላይ ቀለል ያለ ከኳስ ጋር መሰረት ያደረገ ንኪኪ ሲሰራ ቆይቷል።

አጥቂው አቡበከር ናስር እና አማካዩ ሱራፌል ዳኛቸው ምንም እንኳን በመጀመርያው ሁለት የልምምድ ምዕራፍ ላይ በሙሉ አቅማቸው ሲሳተፉ የተመለከትን ቢሆንም በኃላ ላይ ጠንከር ባለው የመጨረሻው ልምምድ ወቅት ከቡድኑ ተገልለው ታይተዋል። ሦስቱም ተጫዋቾች መቼ የቡድኑን ሙሉ ልምምድ ይሳተፋሉ ለሚለው ጥያቄም ከቀናቶች በኃላ እንደሚሰሩ ተነግሮናል።

ጠንከር ያለ በቀን ሁለት ጊዜ የሚከናወነው ልምምዳቸው በቀጣይ ቀናት የሚቀጥል ሲሆን የጨዋታው ቀን መዳረሻ ወቅት ቀለል እያለ ይመጣል ተብሎ ይጠበቃል። በአዳማ በነበረን ቆይታ በቡድኑ ውስጥ ያለው የአንድነት መንፈስ የሚያስደስት ሆኖ ያገኘነው ሲሆን በቀጣይ የቡድኑን ዝግጅትን አለፍ አለፍ እያለን በመቃኘት እና ወቅታዊ መረጃዎችን በማጠናቀር ወደእናተ ማድረሳችንን የምንቀጥል ይሆናል።

ተጨማሪ ምስሎች በኢንስታግራም ገፃችን ከደቂቃዎች በኋላ ያገኛሉ | INSTAGRAM PAGE