ሽመልስ በቀለ የራሱን የግብ ሪከርድ አሻሽሏል

በግብፅ ፕሪምየር ሊግ 32ኛ ሳምንት ኢትዮጵያዊው አማካይ ሽመልስ በቀለ የውድድር ዓመቱን 11ኛ ጎል አስቆጥሯል።

በተለያዩ ምክንያቶች በተበታተነ መልኩ ሲካሄድ የቆየው የግብፅ ፕሪምየር ሊግ የዘንድሮው የውድድር ዓመት ከበርካታ ተስተካካይ ጨዋታዎች መደረግ በኋላ አሁን 32ኛ ሳምንት ላይ ደርሷል። ሊጠናቀቅ ሁለት የጨዋታ ሳምንት ብቻ በቀረው ሊግ ላይም ኢትዮጵያዊው የምስር ለል መቃሳ አማካይ ሽመልስ በቀለ ቡድኑ ትናንት ምሽት ከአል ሞካውሉን ባደረገው ጨዋታ ላይ ተቀይሮ በመግባት አንድ ጎል አስቆጥሯል።

በአል ሞካውሉን 3-2 አሸናፊነት የተጠናቀቀው ጨዋታን በተጠባባቂ ወንበር በመቀመጥ የጀመረው ሽመልስ በሁለተኛው አጋማሽ ጅማሮ ላይ ሳላህ አሾውርን ቀይሮ የገባ ሲሆን በ63ኛው ደቂቃ ቡድኑ ሁለት አቻ የሆነበትን ጎል ማስቆጠር ችሎ ነበር። ሆኖም ከሽመልስ ጎል አምስት ደቂቃዎች በኋላ አህመድ ዳውድ ያስቆጠራት ጎል አል ሞካውሉን ባለ ድል አድርጋለች።

ምስር ለል ማቃሳ በውድድር ዓመቱ ጥሩ ጉዞ ሲያደርግ የነበረ ቢሆንም በተከታታይ ሽንፈቶች ከደረጃው ለመንሸራተት ተገዷል። ካለፉት አስር ጨዋታዎች አንድ ብቻ ድል የቀናው ቡድኑ በ37 ነጥቦች 12ኛ ደረጃ ላይም መቀመጥ ችሏል። ያም ሆኖ ከቡድኑ መንሸራተት በተቃራኒ ሽመልስ በቀለ ጎሎችን ማስቆጠሩን በመቀጠል ከባሳም ሞስሪ ጋር በጋራ የቡድኑ ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪነትን እየመራ ይገኛል።

ሽመልስ በቀለ ትናንት ምሽት ጎል ማስቆጠሩን ተከትሎ የጎል መጠኑን 11 ያደረሰ ሲሆን ይህም በግብፅ ቆይታው በአንድ የውድድር ዘመን ያስቆጠረው ከፍተኛ የሊግ ጎሉ ሆኗል። ከዚህ ቀደም በ2018/19 የውድድር ዓመት በድምሩ 10 ጎሎች (በፔትሮጄት 7፣ በማቃሳ 3) ያስቆጠረ ሲሆን አሁን የራሱን ሪከርድ ሁለት ጨዋታዎች እየቀሩት ማሻሻል ችሏል።

የግብፅ ፕሪምየር ሊግ ከሁለት ጨዋታዎች በኋላ ሲጠናቀቅ ምርስ ለል ማቃሳ ረቡዕ ከፒራሚድ፣ ዓርብ ከስሞሀ ጋር ጨዋታዎች ካደረገ በኋላ ሽመልስ በቀለ ሀገሩ ከጋና እና ዚምባብዌ ለምታደርጋቸው የዓለም ዋንጫ ማጣርያ ጨዋታዎች ብሔራዊ ቡድኑን ይቀላቀላል ተብሎ ይጠበቃል።