አዳማ ከተማ በከፍተኛ ሊጉ ደምቆ የታየውን ተጫዋች ለማስፈረም ተስማምቷል

በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን በአዲስ አበባ ከተማ መልካም የሚባል ዓመት ያሳለፈው የመስመር አጥቂ አዳማ ከተማን ለመቀላቀል ከጫፍ ደርሷል።

አሠልጣኝ ፋሲል ተካልኝን የሾሙት አዳማ ከተማዎች ዘንድሮ የነበረባቸውን ድክመት በመሸፈን በቀጣይ ተጠናቅሮ ለመቅረብ በተጫዋቾች የዝውውር ገበያ ላይ ተሳትፎ እያደረገ እንደሆነ ይታያል። በሁሉም የሜዳ ክፍሎች ላይ አዳዲስ ተጫዋቾችን ያስፈረመው ክለቡም አቡበከር ወንድሙን ወደ ስብስቡ ለመቀላቀል የመጨረሻ ምዕራፍ ላይ መድረሱን ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች።

ከቅዱስ ጊዮርጊስ ታዳጊ ቡድን የተገኘው አቡበከር ለአራዳ ክ/ከተማ፣ ለከፋ ቡና እና ሀላባ ከተማ ተጫውቶ የነበረ ሲሆን ዘንድሮ ደግሞ አዲስ አበባ ከተማን ተቀላቅሎ የእግርኳስ ህይወቱን ቀጥሏል። በውድድር ዓመቱ ስምንት ግቦችን ያስቆጠረው የመስመር አጥቂው ከሰሞኑን ከአዳማ ከተማ ጋር የሚያደርገው ድርድር ፍሬ ማፍራቱን የተገነዘብን ሲሆን ምናልባት ነገ አልያም ከነገ በስትያ ዝውውሩን በይፋ እንደሚያጠናቅቅ ሰምተናል።