👉”እኔ ወደ ቡድኑ ከመጣው ጀምሮ ለመገንባት የምንፈልገው ነገር አለ”
👉”የቡድኑ 70 እና 75 በመቶ የሚሰለፉ ተጫዋቾች ስለሚታወቁ ያን ያህል ጫና አይፈጠርም”
በአሠልጣኝ ውበቱ አባተ የሚመራው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በኳታር አስተናጋጅነት ለሚካሄደው የ2022 ዓለም ዋንጫ ለማለፍ ከደቡብ አፍሪካ፣ ጋና እና ዚምባቡዌ ጋር እንደተደለደለ ይታወቃል። ብሔራዊ ቡድኑ በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ በውድድሩ ለመሳተፍም ካለንበት ወር የመጨረሻ ቀናት ጀምሮ የምድብ ጨዋታዎቹን ከጋና እና ዚምባቡዌ ጋር ማድረግ ይጀምራል። ከፊቱ ላሉበት ወሳኝ ጨዋታዎች ከነሐሴ 4 ጀምሮ አዳማ ላይ መቀመጫውን በማድረግ ሲዘጋጅ የነበረው ቡድኑም ዛሬ ቀትር በዋና አሠልጣኙ አማካኝነት መግለጫ ሰጥቷል። አሠልጣኙም ስለ ዝግጅታቸው፣ ከፊታቸው ስላሉባቸው ሁለት የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዎች እና ስለ አፍሪካ ዋንጫው የምድብ ድልድል ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ወሎ ሰፈር አካባቢ በሚገኘው የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ጽሕፈት ቤት መሰብሰቢያ አዳራሽ በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ አሠልጣኝ ውበቱ አባተ በአዳማ እያሰራው ስላለው ልምምድ በቅድሚያ ገለፃ አድርገዋል። አሠልጣኙ በገለፃቸው እየተሰጡ ያሉት ልምምዶች የአካል ብቃት እና ሥነ-ልቦና ላይ ያተኮሩ መሆናቸውን አውስተው ታክቲካዊ ጉዳዮች ላይም ትኩረት እንደተደረገ አመላክተዋል።
“አዳማ ላይ ልምምዳችንን እያደረግን እንገኛለን። ተጫዋቾቹ በአካል ብቃቱ እና በሥነ-ልቦናው ረገድ ዝግጁ እንዲሆኑም እየጣርን እንገኛለን። እኔ ወደ ቡድኑ ከመጣው ጀምሮ ለመገንባት የምንፈልገው ነገር አለ። ቶሎ ቶሎ ተጫዋቾችንም አለዋወጥንም። በዓመቱ መጀመሪያ ከጠራነው ስብስብ 80 በመቶ የሚሆኑት ተጫዋቾች ያሁኑ ቡድን ላይ አሉ። አለበለዚያ ውድድሮች እና ጨዋታዎች በመጡ ቁጥር አዳዲስ ተጫዋቾችን ከጠራን የምንፈልገውን ቡድን መገንባት አንችልም።
“ከፊታችን ላሉብን ሁለቱ ጨዋታዎች 28 ተጫዋቾችን ጠርተን ነበር። ከጠራናቸው ተጫዋቾች ውስጥ ሀይደር ሸረፋ ቀድሞ በያዘው የጋብሻ ሥነ-ስርዓቱ እንዲሁም ሙጂብ ቃሲም እሱ የሚያስፈልግበት የዝውውር ሂደት ላይ ስለነበረ ከእኛ ጋር ተነጋግረው ጥያቄያቸውን ተቀብለን ከስብስቡ ውጪ እንዲሆኑ አድርገናል። ከዚህ ውጪ ግን ወደ አዳማ እንዳቀናን በመጀመሪያው የልምምድ ቀን ሀብታሙ ተከስተ ከባት ህመም ጋር በተያያዘ ልምምድ አቋርጧል። በጉዳቱ ምክንያት ከስብስቡ ውጪም ሆኗል። እንደሚታወቀው እግርኳስ ለጉዳት ቅርብ የሆነ ስፖርት ነው። ከዚህም መነሻነት አስቻለው ታመነ እና አቡበከር ናስር በፊት የነበረባቸው ጉዳት አገርሽቶ ነበር። ከእነሱ ውጪ ሱራፌል ዳኛቸውም መጠነኛ ጉዳት በልምምድ ላይ አስተናግዶ ነበር። አሁን ግን ተጫዋቾቹ በጥሩ ጤንነት ላይ ይገኛሉ።”
ወሳኝ አህጉራዊ ውድድር ካለባቸው ፋሲል ከነማ እና ኢትዮጵያ ቡና የተመረጡ ተጫዋቾችን በተመለከተ በተከታይ ጥያቄ ቀርቦላቸው ምላሽ መስጠት የቀጠሉት አሠልጣኙ “የአፍሪካ ቻምፒየንስ ሊግ እና ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ጨዋታዎች ከዋናው ብሔራዊ ቡድን ጨዋታ በኋላ ነው የሚመጡት። የማይካደው ነገር በትንሽ ቀናት ልዩነት ለብሔራዊ ቡድኑ እና ለክለባቸው ጨዋታ የሚያደርጉት ተጫዋቾች ጫና ይፈጠርባቸዋል። ግን ምንም ማድረግ አይቻልም። በተቻለ መጠን ጫናውን ለመቀነስ እንጥራለን። ይህ ኢትዮጵያ ላይ ብቻ ሳይሆን ሁሉም ሀገራት ላይ የሆነ ነገር ነው። ማለትም ከመርሐ-ግብር አወጣት ጋር ተያይዞ የተፈጠረ ነገር ነው። እንዳልኩት ምንም ማድረግ አንችልም። ወደፊት ከእንደዚህ አይነት ነገሮች ጋር መላመድ ይኖርብናል።” ብለዋል።
አሠልጣኙ ከዚሁ ሀሳብ ጋር አያይዘው ከክለቦቹ (ፋሲል ከነማ እና ኢትዮጵያ ቡና) ጋር ውይይት እንደተደረገ ጠቁመው ይህ የብሔራዊ ቡድን ግዳጅ እንደሆነ እና ሁለቱን ጨዋታዎች እንዳለቁ ተጫዋቾቹ ወደየ ክለቦቻቸው እንደሚሄዱ አስረድተዋል። በተያያዘ ከጨዋታ መደራረብ ጋር ተያይዞ ብሔራዊ ቡድኑ በጥቂት ቀናት ልዩነት የወዳጅነት ጨዋታዎቹን ጨምሮ አራት ግጥሚያዎችን ማድረጉ ጫና አይኖረውም ወይ ተብለው ተጠይቀው “አራት ጨዋታዎችን በጥቂት ቀናት ልዩነት ማድረግ ጫና አለው። ግን በወዳጅነት ጨዋታዎቹ ላይ ተጫዋቾቹ ላይ ያለውን ጫና ለመቀነስ እና ሁሉም ተጫዋቾች እንዲጋሩት እናደርጋለን። ግን በዋናነት የቡድኑ 70 እና 75 በመቶ የሚሰለፉ ተጫዋቾች ስለሚታወቂ ያን ያህል ጫና አይፈጠርም።” በማለት ምላሽ ሰጥተዋል።
ለ40 ደቂቃዎች ብቻ በቆየው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ለብቻቸው በስፍራው ለተገኙ ጥቂት የብዙሃን መገናኛ አባላት ምላሽ ሲሰጡ የነበሩት አሠልጣኝ ውበቱ አብዛኞቹ ተጫዋቾች ከግንቦት 20 በኋላ (ሊጉ ከተጠናቀቀ በኋላ) ውድድርም ሆነ ቋሚ ልምምድ ላይ ስላልነበሩ በልምምዳቸው ተጫዋቾቹን ለጨዋታ ቶሎ የማብቃት ሥራ ላይ ትኩረት እንደተሰጠ አመላክተዋል። በመግለጫው ላይ ካለው ያነሰ የተጫዋቾች ስብስብ አንፃር አሁን ላይ ቅነሳ እንደማይደረገ ተጠቁሞ ከዚህ በኋላም ለአዲስ ተጫዋችም ጥሪ እንደማይደረግ ተገልጿል። ሽመልስ በቀለ ብቻ ግን የክለብ ጨዋታዎቹን ሲጨርስ ቡድኑን እንደሚቀላቀል ተጠቅሷል።
ብሔራዊ ቡድኑ ሀሙስ እና እሁድ ከሴራሊዮን እና ዩጋንዳ ጋር ስለሚያደርገው የአቋም መፈተሻ ጨዋታዎች ሀሳብ መስጠት የቀጠሉት አሠልጣኙ ጨዋታዎቹ በሁለቱ ሀገራት መልካም ፍቃደኝነት የተገኙ መሆኑን አንስተው ብሔራዊ ፌዴሬሽኑም ከፍተኛ ጥረት እንዳደረገ ተናግረዋል። በተለይ የዩጋንዳው ጨዋታ ሙሉ በሙሉ በኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ጥረት መገኘቱም ሲገለፅ የሴራሊዮን ጨዋታ ደግሞ ፌዴሬሽኑ ከስመጥር ስፖርት እና ኢንተርቴመንት ጋር በጋራ በመሆን የተገኘ መሆኑ ተነግሯል።