ብርቱካናማዎቹ የቅድመ ውድድር ዝግጅት የሚጀምሩበትን ቀን ይፋ አድርገዋል

በአሠልጣኝ ዘማርያም ወልደጊዮርጊስ የሚመሩት ድሬዳዋ ከተማዎች ለ2014 የሊጉ ውድድር ዝግጅት የሚያደርጉበት ቦታ እና የሚጀምሩበት ቀን ታውቋል።

በተጠናቀቀው የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 28 ነጥቦችን በመሰብሰብ አስረኛ ደረጃን ይዞ ያጠናቀቀው ድሬዳዋ ከተማ የአሠልጣኙን ውል ካደሰ በኋላ በዝውውር ገበያው በመሳተፍ ስብስቡን ሲያጠናክር ነበር። ከሌሎቹ የሊጉ ክለቦቸ ቀድሞ የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን ለመጀመር አስቦ የነበረው ክለቡም በተለያዩ ምክንያቶች ቀኑን ገፍቶ የፊታችን ሀሙስ ተጫዋቾቹን እንደሚሰበስብ ለማወቅ ተችሏል።

የክለቡ ተጫዋቾች ሀሙስ ሀዋሳ ላይ እዲሰባሰቡ ከተደረገ በኋላ አጠቃላይ የህክምና ምርመራ ተደርጎላቸው በማግስቱ መደበኛ ልምምዳቸውን እንደሚጀምሩም ተጠቁሟል።