ዋልያዎቹ ከነገው ጨዋታ በፊት የመጨረሻ ልምምዳቸውን ሰርተዋል

በነገው ዕለት ከሴራሊዮን ጋር የአቋም መፈተሻ ጨዋታ የሚያደርገው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የመጨረሻ ልምምዱን ዛሬ አመሻሽ ሰርቷል።

በአሠልጣኝ ውበቱ አባተ የሚመራው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በቀጣይ ዓመት ለሚከናወነው የዓለም ዋንጫ ለማለፍ ከደቡብ አፍሪካ፣ ጋና እና ዚምባቡዌ ጋር እንደተደለደለ ይታወቃል። የአፍሪካ ተወካይ ቡድኖችን የሚለዩት የምድብ ማጣሪያ ጨዋታዎች ከአንድ ሳምንት በኋላ ሲጀምሩ ዋልያውም ወደ ምዕራብ አፍሪካዊቷ ሀገር በማምራት በኬፕ ኮስት ስታዲየም የጋና አቻውን የሚገጥም ይሆናል። ከአምስት ቀን በኋላ ደግሞ ባህር ዳር ላይ የዚምባቡዌ ብሔራዊ ቡድንን የሚፋለም ይሆናል። ታዲያ ለእነዚህ ወሳኝ ጨዋታዎች ከነሐሴ 4 ጀምሮ አዳማ ላይ ዝግጅቱን ሲያደርግ የከረመው ቡድኑም ነገ እና እሁድ ሁለት የአቋም መለኪያ ጨዋታዎችን (ከሴራ ሊዮን እና ዩጋንዳ) የሚያደርገ ይሆናል።

ለእነዚህ ሁለት የአቋም መፈተሻ ጨዋታዎች በትናንትናው ዕለት ወደ ባህር ዳር ያቀናው ስብስቡም ዛሬ ባህር ዳር ላይ ሁለተኛ ከጨዋታው በፊት ደግሞ የመጨረሻ ልምምዱን ከ10:05 ጀምሮ በባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም አከናውኗል።

የሴራሊዮን ብሔራዊ ቡድን ልክ ልምምዱን ሲጨርስ በስፍራው የደረሰው የአሠልጣኝ ውበቱ ስብስብም ለአንድ ሰዓት ከአስራ አምስት ደቂቃ የቆየ ልምምድ ሲሰራ ነበር። መጀመሪያ ላይም ተጫዋቾቹ እንዲያሟሙቁ ከተደረገ በኋላ አራት ቡድን ሰርተው መሐል ባልገባ (በተለምዶ) ሲጫወቱ ነበር። ዋና አሠልጣኙን ጨምሮ የነበረው የመሐል ባልገባ እንቅስቃሴ ከተገባደደ በኋላም ረዳት አሠልጣኙ አስራት አባተ የሜዳ ላይ ተጫዋቾቹን ፍጥነት እና ቅልጥፍና ላይ ያተኮረ አጠር ያለ ሥራ ሲያሰሩ አይተናል።

በመሐል የአጭር ደቂቃ እረፍት የሚሰጣቸው ተጫዋቾችም በመቀጠል በግማሽ ሜዳ የተገደበ ጨዋታ እንዲያደርጉ ሆኗል። በዚህ መርሐ-ግብር ላይ የማጥቃት ባህሪ ያላቸው ተጫዋቾች የመከላከል ባህሪ ካላቸው ተጫዋቾች ጋር በተቃራኒ እንዲፋሉ ተደርጓል። በዋናነት ደግሞ አብዛኛውን የጨዋታ ክፍለ ጊዜ በተጋጣሚ ሜዳ የሚያሳልፉት አጥቂ እና የአጥቂ አማካዮች ተናበው ግብ ማስቆጠር የሚችሉበት እንዲሁም ተከላካዮች በተደራጀ መንገድ ጥቃቶችን የሚመክቱበትን ስልት አሠልጣኙ ሲያሳዩ ታዝበናል።

በዛሬው ልምምድ ላይ የቡድኑ አምበል ጌታነህ ከበደ በትናንትናው ዕለት በግራ እግሩ ላይ በተሰማው ህመም ምክንያት ከአጋሮቹ ጋር ልምምድ ሲሰራ አልነበረም። ይልቁንም ለብቻው ተነጥሎ ቀለል ያሉ እንቅስቃሴዎችን ሲያደርግ አይተናል። የተጫዋቹ ጉዳት ያን ያህል ባይሆንም ምናልባት ነገ ጠዋት በሚኖር ምርመራ በጨዋታው የመሰለፉ እና አለመሰለፉ ጉዳይ እንደሚለይ ሰምተናል። ነገርግን ተጫዋቹን ቶሎ ወደ ጨዋታ አስገብቶ ሌላ ጉዳት እንዳያስተናግድ ነገ እረፍት ሊሰጠው እንደሚችልም ተገምቷል።

የተሻለ መናበብ ከታየበት ልምምድ በኋላ ደግሞ ከሁለቱ መስመሮች የቆሙ ኳሶችን መለማመድ ተይዟል። አጥቂዎቹ ግብ ለማግባት ተከላካዮቹ ደግሞ ለማውጣት ሲጥሩ ከነበረበት እንቅስቃሴ በኋላ አቡበከር ናስር፣ አቤል ያለው እና አማኑኤል ገብረሚካኤል በተናጥል የፍፁም ቅጣት ምት ሲለማመዱ አስተውለናል። ልምምዱም 11:20 ሲል ፍፃሜውን አግኝቷል። ጥሩ የቡድን መንፈስ ላይ እንዳለ የታየው ብሔራዊ ቡድኑም ነገ ዘጠኝ ሰዓት ጨዋታውን የሚያደርግ ይሆናል።

በተያያዘ ዜና ሶከር ኢትዮጵያ ባገኘችው መረጃ መሠረት የነገው የኢትዮጵያ እና ሴራሊዮን ጨዋት በዝግ ስታዲየም ያለ ተመልካች የሚደረግ ይሆናል። ይህ በእንዲህ እንዳለ ጨዋታው የቀጥታ የቴሌቪዥን ስርጭት እንደማያገኝም ተጠቁሟል።