“ኬንያ ድረስ ተጉዘን እንደ ቱሪስት ሀገር አይተን ብቻ አንመለስም፤ እኔም ሆነ ተጫዋቾቼ የተሻለ ነገር ለማምጣት ተዘጋጅተናል” ብርሃኑ ግዛው

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዋና አሠልጣኝ ብርሃኑ ግዛው ከፊቱ ስላለበት የአፍሪካ ቻምፒየንስ ሊግ የማጣሪያ ውድድር እና ስለ ዝግጅቱ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ቆይታ አድርጓል።

የወቅቱ የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አሸናፊው ክለብ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በሚካሄደው የአፍሪካ የሴቶች ቻምፒየንስ ሊግ ውድድር ላይ ለመሳተፍ የሴካፋ ዞን የማጣሪያ ጨዋታዎችን ማከናወን እንዳለበት ይታወቃል። የአራት ጊዜ የሊጉ አሸናፊ ንግድ ባንክ ስምንት የቀጠናው ክለቦችን ተሳታፊ በሚያደርገው ውድድር ላይ ለመሳተፍም ከሰኔ 25 ጀምሮ የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን ቢሾፍቱ ከተማ ላይ መቀመጫውን በማድረግ ሲሰራ የቆየ ሲሆን ዛሬ ከሰዓት ግን ወደ አዲስ አበባ ተጉዟል። ስብስቡ 21 ተጫዋቾችን፣ ስድስት የአሠልጣኝ ቡድን አባላትን እና የአስተዳደር ሰው በመያዝ ነገ 5:10 ወደ ኬንያ ከማምራቱ በፊትም አሠልጣኝ ብርሃኑ ግዛውን ሶከር ኢትዮጵያ አግኝታ ስላሳለፉት የዝግጅት ጊዜ፣ ስለኬኒያው ውድድር እና ተያያዥ ጉዳዮች ተከታዩን ቆይታ አድርጋለች።

በኬንያ አስተናጋጅነት ለሚካሄደው የማጣሪያ ውድድር ስላደረጉት ዝግጅት?

እንደሚታወቀው የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ መጋቢት 19 ነበር የተጠናቀቀው። እኛ ደግሞ ሰኔ 25 ነው ለዚህ ዝግጅት የተሰባሰብነው። ይህ ቢሆንም ውድድሩ ከአንድም ሦስት ጊዜ ተራዝሞ ነበር። ይህንን ተከትሎም በመሐል ተጫዋቾቻችንን ለእረፍት ወደየቤታቸው እንዲሄዱ አድርገን ነበር። ከዛም የውድድሩ መጀመሪያ ቀን እንደ አዲስ ሲታወቅ በድጋሜ ጠርተናቸው ልምምዳችንን መስራት ቀጥለናል። በተቻለው አቅም በፍቅር፣ በሠላም እና በደስታ ልምምዳችንን ብንሰራም ዝግጅታችን በቂ ነበር ግን ማለት አልችልም። ምክንያቱም የአቋም መለኪያ ጨዋታ ማድረግ ሲገባን ስላላደረግን። በልምምድ በሚታይ ነገር ብቻ ተጫዋቾችን አትለይም። ጨዋታ ራሱን የቻለ ትልቅ መድረክ ነው። ይህ ቢሆንም ግን የሚገጥመን ቡድን ሳናገኝ ቀርተናል። በተወሰነ መልኩ ይህ ጉዳይ ስጋት ቢጭርብኝም በተጫዋቾቼ ተነሳሽነት ግን ደስተኛ ነኝ። በአጠቃላይ እየተደማመጥንም ስለነበር ዝግጅታችንን ስንሰራ የነበረው በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በሚደረገው ውድድር ላይ ጥሩ ውጤት ለማምጣት እንሞክራለን።

የሴቶች ፕሪምየር ሊግ ከተጠናቀቀ ዘለግ ያሉ ቀናት ተቆጥረዋል። ይህንን ተከትሎም ተጫዋቾቹ ከቤታቸው ነው የመጡት። ከዚህ ጋር ተያይዞ ተጫዋቾቹን በቶሎ ለጨዋታ ማዘጋጀት አልቸገረክም?

ምንም ጥያቄ የለውም። እጅግ በጣም ፈታኝ ነበር። ተጫዋቾች በግላቸው እንኳን ቢሰሩ አጥጋቢ ሥራ ይሰራሉ ማለት አይደለም። ከአሠልጣኝ ጋር በሚሰሩበት ጊዜ እየተቆጣጠርናቸው ስለሚሰሩ የተሻለ ነገር ይፈጠራል። አይደለም ሦስት እና አራት ወር አስራ አምስት ቀን ያረፈ ሰውነት ራሱ ያስቸግራል። እንዳልኩት አዳጋች ነበር ግን በተቻለ መጠን የተሻለ ነገር ለመፍጠር ጥረት አድርገናል።

የቅድመ ውድድር ዝግጅት አይነት ልምምድ እንደነበረ እረዳለሁ። ግን በዋናነት ምን አይነት ነገር ላይ ትኩረት ሰጥታችሁ ስትለማመዱ ነበር?

በመጀመሪያዎቹ 15 ቀናት ቡድኑን ለማዘጋጀት ነበር ስንጥር የነበረው። ቡድን ሲዘጋጅ ደግሞ አካላዊ ብቃት፣ ቴክኒክ እና ታክቲክንም ያካተተ ሥራ ይጠበቅብካል። በጥሩ ሁኔታ ያልኩትን ነገር ለማምጣት ደግሞ ከ6-8 ሳምንት ያስፈልጋል። እኛ ግን ይህ ጊዜ ስላልነበረን ትንች ስንቸገር ነበር። ነገርግን ውድድሩ ተራዘመ ከተባለ በኋላ በነበሩት 15 ተጨማሪ ቀናት በተሻለ ሁኔታ ያሰብነውን ነገር ለማምጣት ጥረናል። ስለዚህ ቡድኑን የማዘጋጀት ስራ ላይ ነበር ትኩረት ሰጥተን ስንሰራ የነበረው። በምስራቅ አፍሪካ ደረጃ ያለ ተቋም እንደ ቀልድ ውድድሩን ሲያራዝም እና ሲገፋ ነበር። ይህ ደግሞ በሥነ-ልቦናው ረገድ ጎድቶናል። የሆነው ሆኖ 43 የልምምድ ቀናትን አሳልፈናል። ተጫዋቾቹም ላይ ሆነ እንደ ቡድን የማየው ነገር የተሻለ ነው።

በውድድሩ እስከ ምን ርቀት ለመጓዝ ታስባላችሁ?
እኔ በህይወቴ ግብ አስቀምጬ ነው የምንቀሳቀሰው። የሴቶች ክለቦችም በሀገራችን እንደሚበራከቱ ከበፊት ጀምሮ አስብ ነበር። ይህም ተሳክቷል። ከዚህ ውጪ ብሔራዊ ቡድን ገብቼ በሙያዬ ሥራ ሰርቻለሁ። በምስራቅ አፍሪካ፣ በአፍሪካ ዋንጫም ሆነ በኦሊምፒክ ውድድር ላይ ተሳትፌያለሁ። አሁን የቀሩኝ ግቦች ሁለት ናቸው። አንዱ በብሔራዊ ቡድን ዓለም ዋንጫ መድረስ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ከክለቤ ጋር በአፍሪካ መድረክ ሻምፒዮን መሆን ነው። ሁለቱም ደግሞ በሂደት ይመጣሉ ብዬ አስባለሁ። እኔም ሆንኩ ተጫዋቾቼ እዚህ ደረጃ እንድንደርስ የሆነው ከአነሳሳችን ጀምሮ ስለለፋን ነው። ኬኒያ ድረስ ተጉዘን እንደ ቱሪስት ሀገር አይተን ብቻ አንመለስም። እግርኳስ ለመጫወት ነው የምንሄደው። የሚገጥመንን ቡድንም በተቻለን አቅም እያሸነፍን የመጣውን ነገር ለመቀበል ዝግጁ ነን። እኔ እና ተጫዋቾቼ እስከ መጨረሻው ድረስ ተጉዘን ሻምፒዮን ለመሆን ተዘጋጅተናል።

በዞኑ ስለምትገጥሟቸው ቡድኖች የምታውቀው ነገር አለ?

ይህ ከባድ ነው። ክለቦቹ የመጡበትን ሀገር ነው የምታውቀው እንጂ እነሱን ከዚህ በፊት ስላላየህ አታውቃቸውም። ከዚህም መነሻነት እዛ ሄደን ነው የክለቦቹን አጨዋወት የምናየው።