የዩጋንዳ ብሔራዊ ቡድን ባህር ዳር ደርሷል

የፊታችን እሁድ ከዋልያዎቹ ጋር የአቋም መፈተሻ ጨዋታ የሚያደርገው የዩጋንዳ ብሔራዊ ቡድን ከደቂቃዎች በፊት ባህር ዳር ደርሷል።

በሰርቢያዊው የቀድሞው የቅዱስ ጊዮርጊስ አሠልጣኝ ሰርዲዮቪች ሚሉቲን ሚቾ የሚመራው የዩጋንዳ ብሔራዊ ቡድን ለኳታሩ የዓለም ዋንጫ ለማለፍ በምድብ አምስት ከማሊ፣ ኬኒያ እና ሩዋንዳ ጋር በመደልደል የማጣሪያ ጨዋታዎችን እንደሚያደርግ ይታወቃል። ብሔራዊ ቡድን በተለይ ከኬንያ እና ማሊ ጋር ላሉበት የምድብ የመጀመሪያ ጨዋታዎች ዝግጅቱን ከቀናት በፊት የጀመረ ሲሆን ለጨዋታዎቹም ይረዳው ዘንድ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ጋር የአቋም መፈተሻ ጨዋታ የፊታችን እሁድ ያከናውናል።

ለእሁዱ ጨዋታም 20 ተጫዋቾችን እንዲሁም አስር የአሠልጣኝ ቡድን አባላት እና አመራሮችን በመያዝ ከደቂቃዎች በፊት ባህር ዳር አየር ማረፊያ የደረሰው ብሔራዊ ቡድኑም በኦሊቭ ሆቴል ማረፊያውን እንደሚያደርግ ተመላክቷል። ቡድኑም ዛሬ ከቀትር በኋላ ቀለል ያለ ልምምድ በባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም የመለማመጃ ሜዳ እንደሚሰራ ተጠቁሟል።

በተያያዘ ዜና እሁድ ከኢትዮጵያ አቻቸው ጋር የአቋም መለኪያ ጨዋታ የሚያደርጉት ዩጋንዳዎች በአፍሪካ ቻምፒየንስ ሊግ ለመወዳደር የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታዎች ከፊቱ ከሚጠብቁት ፋሲል ከነማ ጋር ሌላ የወዳጅነት ጨዋታ እንዲያደርጉ ጥረት እየተደረገ እንደሆነ ሰምተናል።