ዋልያዎቹ በአቋም መፈተሻ ጨዋታ አቻ ተለያይተዋል

በዛሬው ዕለት ከሴራሊዮን ጋር የአቋም መፈተሻ ጨዋታ ያደረገው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ግጥሚያውን ያለ ግብ አጠናቋል።

ገና ጨዋታው እንደተጀመረ በግራ መስመር ወደ ሴራሊዮን የግብ ክልል ያመሩት ዋልያዎቹ ረመዳን የሱፍ ለታፈሰ ሠለሞን አቅብሎት ታፈሰ ለጥቂት በወጣበት ኳስ በጊዜ መሪ ሊሆኑ ነበር። በጅማሮ ተጋጣሚያቸውን ማስደንገጥ የያዙት የአሠልጣኝ ውበቱ አባተ ተጫዋቾች በአምስተኛው ደቂቃም የሰላ ጥቃት ፈፅመው ነበር። በዚህ ደቂቃም በጨዋታው የመሐል አጥቂ ሆኖ የነበረው አማኑኤል ገብረሚካኤል ከመስዑድ የተቀበለውን ኳስ በጥሩ ሁኔታ ወደ ግብነት ለመቀየር ቢጥርም ሳይሳካለት ቀርቷል።

ወደ ራሳቸው የግብ ክልል ተጠግተው የዋልያዎቹን ጥቃት መመከት ላይ ተጠምደው ያሳለፉት ሴራሊዮኖች እስከ 18ኛው ደቂቃ ድረስ አንድም ሙከራ አላደረጉም ነበር። በተጠቀሰው ደቂቃ እነርሱ ሙከራ ከማድረጋቸው ከአንድ ደቂቃ በፊት ግን የተከላካይ አማካዩ ይሁን እንዳሻው ከሳጥኑ ጫፍ አክርሮ በመምታት ግብ ሊያስቆጥር ነበር። ይህ ሙከራ ወደ ግብነት ሳይቀየር ቀርቶ ወደ ኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የግብ ክልል ለመጀመሪያ ጊዜ የመጡት ሴራሊዮኖች ደግሞ በፎፋና ሰዒዱ አማካኝነት ጥቃት ቢፈፅሙም የተክለማርያም ሻንቆን መረብ ማግኘት አልቻሉም።

ወደ ፍፁምነት የተጠጋ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ የነበረው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በግማሽ ሰዓት ላይ በአማኑኤል አማካኝነት የግብ ዘቡ ካማራ ሙሐመድን የፈተነ ኳስ ወደ ግብ ልኮ ነበር። ነገርግን ኳሱ መረብ ላይ ሳያርፍ ቀርቷል። የመጀመሪያው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜም ያለ ግብ አቻ ተጠናቆ ተጫዋቾች ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

በሁለተኛው አጋማሽ ተሻሽለው ወደ ሜዳ የገቡ የሚመስለው ሴራሊዮኖች እንደ መጀመሪያው ግማሽ አፈግፍጎ መጫወታቸውን ትተው ቀዳሚ የሚሆኑበትን ዕድል ፍለጋ መታተር ይዘዋል። በዋናነት ደግሞ ቡድኑ ረጃጅም ኳሶችን እና የቆሙ ኳሶችን ወደ ግብነት ለመቀየር ሲሞክር ታይቷል። አጋማሹ በተጀመረ በስድስተኛው ደቂቃም ቡድኑ የመዓዘን ምት አግኝቶ የነበረ ሲሆን አጋጣሚውን ጃቢ ካሊፋ እጅግ በጥሩ ሁኔታ ወደ ግብነት ለመቀየር ጥሮ ነበር።

በአጋማሹ አከታትለው በለወጧቸው ተጫዋቾች ይበል እየጠነከሩ የመጡት ሴራሊዮኖች በ66ኛው ደቂቃ በባጉራ አቡበከር አማካኝነት ሌላ ሙከራ አድርገው ነበር። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾች እንደ መጀመሪያው አጋማሽ ከኳስ ጋር ያላቸውን ጊዜ ባያራዝሙም የኳስ ቁጥጥር የበላይነታቸውን አልተነጠቁም። በ68ኛው ደቂቃም ቡድኑ በአማኑኤል አማካኝነት መዓዘን ምትን መነሻ ባደረገ ኳስ መሪ ለመሆን ዳድቶ ነበር። ሙሉ የጨዋታ ክፍለ ጊዜው ሊጠናቀቅ ሁለት ደቂቃዎች ሲቀሩትም ተቀይሮ የገባው ደስታ ዩሐንስ ከፍፁም ዓለሙ የደረሰውን ኳስ በመሞከር ቡድኑን አሸናፊ ለማድረግ ቢጥርም ግብ ጠባቂው እንደምንም አውጥቶበታል። የጨዋታውን ማብቂያ የዕለቱ አልቢትር ለሚ ንጉሴ ሊያሰሙ ደቂቃ ሲቀረውም ዱምቡያ አቡ በሰከንዶች ልዩነት በሰራቸው ጥፋቶች ከሜዳው በቀይ ካርድ ተሰናብቷል። ጨዋታውም ያለ ግብ 0-0 ፍፃሜውን አግኝቷል።

ጨዋታው ከተጠናቀቀ በኋላ የአቋም መለኪያ ግጥሚያው ላይ በቋሚነት ያልተሰለፉት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾች እና ተቀይረው የገቡ ተጫዋቾች (በአጠቃላይ 16 ተጫዋቾች) ለአንድ ሰዓት የቆየ ልምምድ ሲሰሩ አስተውለናል። ስብስቡም የግማሽ ሜዳ ግጥሚያ አድርጎ ወደ አረፈበት ሆቴል አምርቷል። በልምምዱ ላይ ግራ እግሩ ላይ ባጋጠመው ጉዳት ከዛሬው ጨዋታ ውጪ የነበው የቡድኑ አምበል ጌታነህ ከበደ ከአጋሮቹ ጋር በመሆን ልምምድ ቢጀምርም ከዛ ግን አቋርጦ ወጥቷል።