ሀዋሳ ከተማ የትጥቅ አቅርቦት ውል ተፈራርሟል

ጎፈሬ የስፖርት ትጥቅ አምራች ከሀዋሳ ከተማ እና ከክለቡ አንድ ወጣት ተጫዋች ጋር አብሮ መስራት የሚያስችለውን ውል ተፈራርሟል።

ሀገር በቀል የትጥቅ አምራች የሆነው ጎፈሬ ከቀናት በፊት ለሲዳማ ቡና ስፖርት ክለብ ትጥቆችን ለማቅረብ ውል ያሰረ ሲሆን ዛሬ ደግሞ ከሀዋሳ ከተማ ጋር አብሮ ለመስራት ተፈራርሟል። ዕኩለ ቀን ላይ በድርጅቱ ቢሮ በተደረገው መርሐ ግብር በሀዋሳ ከተማ ስፖርት ክለብ በኩል ሥራ አስኪያጁ አቶ ሁቴሳ ኡጋሞ በጎፈሬ የስፖርት ትጥቅ አምራች በኩል ደግሞ አቶ ሳሙኤል መኮንን ሁለቱ አካላት አብረው መሥራት መጀመራቸውን የሚያበስረውን ውል ተፈራርመዋል።

እስከ 2.8 ሚሊየን ብር በሚገመተው እና የሦስት ዓመት ርዝማኔ ባለው የሁለቱ ወገኖች ስምምነት ጎፈሬ በመጀመሪያ ዙር አስር ሺህ ትጥቆችን ለክለቡ እንደሚያቀርብ ተነግሯል። ትጥቆቹ ከዋናው ቡድን በተጨማሪ በአራት የዕድሜ እርከን ቡድኖች በሁለቱም ፆታዎች እንዲሁም ስፖርት ክለቡ የሚሳተፍባቸውን ሌሎች የግል እና የቡድን ስፖርቶች የሚያካትት ነው። የትጥቅ አቅርቦቱ ሁለት ዓይነት ከሆኑት የመጫወቻ መለያዎች በተጨማሪ የልምምድ፣ የተጠባባቂ ተጫዋቾች፣ የመመገቢያ እንዲሁም የጉዞ ማለያዎችን ያካትታል። ከዚህ በተጨማሪ ሁለቱ አካላት የደጋፊ ማልያ ሽያጭን በተመለከቱ የማርኬቲንግ ስትራቴጂዎችም አብረው እንደሚሰሩ ተነግሯል።

በክለቡ እና በትጥቅ አምራቹ ጋር ከተደረገው ስምምነት በተጨማሪ ከዚህ ቀደም ባልተለመደ መልኩ ጎፈሬ የሀዋሳውን ወጣት አማካይ ወንድምአገኝ ኃይሉን የድርጅቱ ብራንድ አምባሳደር በማድረግ ለቀጣዮቸ ሁለት ዓመታት አብሮ ለመስራት ተፈራርሟል። በስምምነታቸው መሰረት ተጫዋቹ የድርጅቱን ትጥቆች እንደሚያተዋውቅ ሲገለፅ በውላቸው ወቅትም ጎፈሬ ለተጫዋቹ በየጊዜው ትጥቆችን የሚያቀርብለት ሲሆን በአንፃሩ ጎፈሬ የተጨዋቹን ስም በዶክመንተሪዎች እና ሌሎች መንገዶች የማስተዋወቅ ፣ የተጨዋቹን ችሎታ የሚያሻሽሉ እገዛዎች ማድረግ እና በየሦስት ወሩ መጠኑ ያልተጠቀሰ ክፍያ እንደሚፈፅምለት ተጠቅሷል።