በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር ሥር የሚከናወን አዲስ ውድድር በ2014 እንዲጀመር ተወስኗል።
” የኢትዮጵያ አንድነት ዋንጫ ” የሚል መጠርያ የሚኖረው ይህ ውድድር በአምስት የኢትዮጵያ አቅጣጫዎች (ሠሜን፣ ደቡብ፣ መካከለኛ፣ ምሥራቅ እና ምዕራብ) በሚል ተከፍሎ አሰልጣኞችን በመመደብ እና አቅጣጫዎቹ በሚያቅፏቸው አካባቢዎች የሚገኙ ተጫዋቾችን በመምረጥ አንድ ቦታ ላይ ውድድር ይደረጋል ተብሏል።
ወጪው በአክሲዮን ማኅበሩ የሚሸፈነው ይህ ውድድር በ2014 ሀዋሳ ላይ እንደሚካሄድ የተገለፀ ሲሆን የአፍሪካ ዋንጫ በሚካሄድበት ወቅት የሊጉ ውድድር ስለማይኖር በዛ ወቅት ላይ ይከናወናል ተብሏል።
የማኅበሩ ሰብሳቢ መቶ ዓለቃ ፈቃደ ማሞ ያቀረቡት ይህ ሀሳብ በጉባዔው ተሳታፊ የፀደቀ ሲሆን ዝርዝር ጉዳዮች ወደ ፊት ይገለፃሉ ተብሎ ይጠበቃል።
በተያያዘ ዜና ለሀገር መከላከያ ሠራዊት ድጋፍ እንዲውል ከአስራ ስድስቱም ክለብ የወደፊት ገቢ ላይ በሚታሰብ መልኩ 500 ሺህ ብር (በአጠቃላይ 8 ሚልየን ብር) ወጪ እንዲደረግ ለጠቅላላ ጉባዔ ቀርቦ ፀድቋል።