መከላከያ የግራ መስመር ተጫዋች አስፈርሟል

ስብስቡን እያጠናከረ የሚገኘው መከላከያ የግራ መስመር ተጫዋች የግሉ ማድረጉ ታውቋል።

በአሠልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ የሚመራው መከላከያ ወደ ሊጉ ማደጉን ካረጋገጠ በኋላ ራሱን ለማጠናከር በዝውውር ገበያው ላይ በንቃት እየተሳተፈ ይገኛል። ከቀናቶች በፊት ቢሾፍቱ ላይ የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን የጀመረው ክለቡም ለአንዳንድ ክለብ አልባ ተጫዋቾች የሙከራ ጊዜ መስጠቱ ሲታወቅ በዚህ የሙከራ ጊዜም አሠልጣኙን ያሳመነው ቢኒያም ላንቃሞ በቋሚ ውል ክለቡን መቀላቀሉ ተገልጿል።

ከሲዳማ ቡና ወጣት ቡድን ወደ ዋናው ቡድን አድጎ ያለፉትን ሦስት ዓመታት በክለቡ የቆየው ቢኒያም በተጠናቀቀው ግማሽ የውድድር ዓመት ላይ በአዲሱ የክለቡ አሠልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ ተቀንሶ እንደነበር አይዘነጋም። አሁን ግን በመከላከያ ባገኘው የሙከራ ጊዜ ራሱን በማሳየት የጦሩን መለያ ለአንድ ዓመት ለመልበስ በይፋ ፊርማ አኑሯል።