ሽመልስ በቀለ ወደ አዲስ ክለብ አምርቷል

በዚህ ሳምንት ከግብፁ ክለብ ምስር ለል መቃሳ ጋር መለያየቱ የተሰማው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አማካይ ወደ አዲስ ክለብ ተዘዋውሯል።

ለፔትሮጀት ፊርማውን በማኖር ከሰባት ዓመታት በፊት ለመጀመሪያ ጊዜ በግብፅ እግርኳስ ብቅ ያለው ሽመልስ በቀለ ዘለግ ላለ ዓመት (ስድስት) በክለቡ ቆይቶ 2019 ላይ ሌላኛውን የሀገሪቱ ክለብ ምስር ለል መቃሳን ተቀላቅሎ እንደነበር ይታወቃል። ሶከር ኢትዮጵያ የግብፅ ብዙሃን መገናኛዎችን ዋቢ አድርጋ ከሁለት ቀናት በፊት ባስነበበችው ዘገባ ቀሪ የአንድ ዓመት ውል የነበረው አማካዩ ከክለቡ ጋር በስምምነት መለያየቱን ይጠቁም ነበር።

አሁን በተገኘ መረጃ ደግሞ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ጋር በአሁኑ ሰዓት የሚገኘው ሽመልስ ወደ ሌላኛው የሀገሪቱ ክለብ ኤልጎውና መዘዋወሩ ያመላክታል። ሌላው ኢትዮጵያዊ አማካይ ጋቶች ፓኖም ከዚህ ቀደም ተጫውቶ ያሳለፈበት ኤል ጎውና ከደቂቃዎች በፊት ዝውውሩን እንዳጠናቀቀም በትዊተር ገፁ ይፋ አድርጓል። ክለቡ አያይዞም “በግብፅ ሊግ ከተጫወቱ ምርጥ የውጪ ዜጎች አንዱ የሆነው ሽመልስ በቀለ ክለባችንን ተቀላቅሏል” ሲል በገፁ አስታውቋል።