አዲስ አበባዎች የቀድሞ ግብ ጠባቂያቸውን አስፈርመዋል

አዲስ አዳጊው ክለብ የቀድሞ ግብ ጠባቂውን በአንድ ዓመት ውል ወደ ስብስቡ ቀላቅሏል።

ወደ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የተመለሱት አዲስ አበባ ከተማዎች በዛሬው ዕለት በይፋ አዳዲስ ተጫዋቾችን ማስፈረም ጀምረዋል። ከደቂቃዎች በፊትም ግብ ጠባቂው ዳንኤል ተሾመን በአንድ ዓመት ውል ማስፈረማቸውን ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች።

ከዚህ ቀደም አዲስ አበባ ከተማን ያገለገለው ዳንኤል 2010 ላይ አዳማ ከተማን ተቀላቅሎ የእግርኳስ ህይወቱን እንደቀጠለ ይታወቃል። በክለቡ በነበሩት የውጪ ግብ ጠባቂዎች ምክንያት በታሰበው መልኩ የቋሚነት ዕድል ሳያገኝ የቆየው ግብ ጠባቂው ዘንድሮ የተሻለ የመጫወት እድል ከማግኘቱ በተጨማሪ ሁለተኛ አምበል ሆኖ እንደነበርም ይታወሳል። አሁን ደግሞ ዳግም ወደ ቀድሞ ክለቡ የሚመልሰውን ዝውውር ከደቂቃዎች በፊት ፈፅሟል።