የኢትዮጵያ ቡና ተጋጣሚ ማለዳ አዲስ አበባ ይደርሳል

በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ የቅድመ ማጣሪያ የመልስ ጨዋታ ኢትዮጵያ ቡናን በባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም የሚገጥመው የዩጋንዳው ክለብ ዩ አር ኤ ነገ ማለዳ ኢትዮጵያ ይገባል።

በካፍ ሥር የሚደረገው እና የአህጉሪቱ ሁለተኛው ትልቁ የክለቦች ፍልሚያ በሆነው የኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ውድድር ላይ ለመሳተፍ ኢትዮጵያ ቡና የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታዎች እያደረገ እንደሆነ ይታወቃል። ባሳለፍነው ሳምንት መጨረሻም ክለቡ በመጀመሪያ ዙር የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታ ወደ ዩጋንዳ አምርቶ የመጀመሪያ መርሐ-ግብሩን አድርጎ 2-1 ተሸንፎ የተመለሰ ሲሆን የመልስ ጨዋታውን ደግሞ የፊታችን እሁድ መስከረም 9 በባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም የሚያከናውን ይሆናል።

በስቴቨን ሙኩዋላ ሁለት ጎሎች በሜዳቸው ድል ተቀዳጅተው የመልሱን ጨዋታ የሚጠባበቁት ዩ አር ኤ’ዎች ነገ ለንጋት አጥቢያ 11 ሰዓት አዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ ዐየር ማረፊያ እንደሚደርሱ ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች። ተጫዋቾች እና የአሠልጣኝ ቡድን አባላትን አካቶ 35 ግለሰቦች ያሉበት የልዑካን ቡድንም ወደ ኢትዮጵያ እንደሚመጣ ታውቋል። የቡድኑ አባላት 11 ሰዓት አዲስ አበባ ከደረሱ በኋላም ወደ ባህር ዳር በሚደረገው የመጀመሪያ በረራ ጨዋታው ወደሚደረግበት ስፍራ እንደሚያመሩ ተነግሮናል። ማለዳ አዲስ አበባ ከሚደርሰው ልዑክ ውጪ የማረፊያ ቦታዎችን ለማመቻቸት ሁለት ሰዎች ዛሬ ባህር ዳር እንደገቡም ድረ-ገፃችን ተረድታለች።

ያለ ዋና አሠልጣኙ እየተመራ ጨዋታውን የሚቀርበው ኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎችን በስታዲየም ማስገባት እንደማይችል የተጠቆመ ሲሆን ልዑካን ቡድኑም እንደ ተጋባዡ ክለብ ነገ 5 ሰዓት ወደ ባህር ዳር እንደሚያመራ ሰምተናል። ቡድኑም ማረፊያውን በአዲስ አምባ ሆቴል ሆቴል በማድረግ የእሁዱን ጨዋታ የሚጠባበቅ ይሆናል።