ከመስከረም 15-30 ድረስ የሚካሄደው የመዲናው የዋንጫ ውድድር ላይ የሚካፈሉ ክለቦች ዛሬ የደንብ ውይይት ሲያደርጉ የእጣ ማውጣት መርሐ-ግብሩም በነገው ዕለት የሚከናወን ይሆናል።
ዘንድሮ ለ15ኛ ጊዜ የሚከናወነው የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ውድድር ከመስከረም ወር አጋማሽ ጀምሮ ለሁለት ሳምንታት በአበበ ቢቂላ ስታዲየም እንደሚደረግ መገለፁ ይታወሳል። ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ኢትዮጵያ ቡና፣ አዲስ አበባ ከተማ፣ መከላከያ፣ ወልቂጤ ከተማ፣ አዳማ ከተማ እና ባህር ዳር ከተማ ተጋባዡን የደቡብ ሱዳን ክለብ ሙኑኪ ኤፍ ሲ’ን ጨምረው በአይነቱ ልዩ የሆነ ውድድር እንደሚሆን የሚጠበቀውን ፍልሚያ የሚያከናውኑ ይሆናል።
ስማቸው ከላይ የተጠቀሱት ክለቦችም በዛሬው ዕለት የውድደሩ ደንብ ዙሪያ ውይይት አድርገዋል። ከፕሮግራም በትክክል አለመገለፅ ጋር በተያያዘ በውይይቱ ካልተገኘው የመከላከያ ክለብ ተወካይ እና ከደቡብ ሱዳኑ ሙኑኪ ክለብ ተወካይ ውጪ ያሉት የክለብ አመራሮች ከረፋዱ 4 ሰዓት ጀምሮ በኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የመሰብሰቢያ አዳራሽ በውድድር እና ሥነ-ስርዓት ኮሚቴው የቀረበው ደንብ ላይ ውይይት አድርገዋል። በውይይቱ ላይ የተለያዩ ሀሳቦች እንደ ግብዐት የተወሰዱ መሆናቸው ሲመላከት በነገው ዕለት በሚኖረው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይም ማብራሪያ እንደሚሰጥባቸው ተነግሮናል።
ነገ ከ8 ሰዓት ጀምሮ በቤስት ዌስት ፕላስ ሆቴል ከሚሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ጎን ለጎን ደግሞ ሁሉም የክለብ ተወካዮች በተገኙበት የእጣ ማውጣት መርሐ-ግብር የሚከናወን ይሆናል። ከሰባቱ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ክለቦች በተጨማሪም ሙኒኪ ኤፍ ሲ ተወካይ እንደሚልክ እንደሚጠበቅም ሰምተናል።
በጤና ሚኒስቴር እና በኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን በሚቀመጠው አቅጣጫ መሠረት ደጋፊዎችን ወደ ስታዲየም የሚመልሰው ይህ ውድድር የቀጥታ የቴሌቪዥን ስርጭት እንዲኖረው እየተሰራ እንደሆነ ድረ-ገፃችን ያገኘችው መረጃ ያመላክታል። ምንም እንኳን ፌዴሬሽኑ ከዲ ኤስ ቲቪ ጋር ውይይቶችን እያደረገ ቢሆንም የአዲስ ሚዲያ ኔትወርክ በአዲስ ቲቪ አማራጩ ውድድሩን በቀጥታ ለማስተላለፍ የመጨረሻ ምዕራፍ ላይ መኮኑንም ተረድተናል።