የሲዳማ ዋንጫ ውድድር የስያሜ ባለ መብት አግኝቷል

ለመጀመሪያ ጊዜ ከመስከረም 16 ጀምሮ የሚካሄደው ውድድር ጎፈሬ የሲዳማ ዋንጫ በሚል ስያሜ እንደሚካሄድ በዛሬው ዕለት በተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ ተገልጿል።

ከተቋቋመ ገና አንድ ዓመቱን ያስቆጠረው የሲዳማ እግርኳስ ፌዴሬሽን በስሩ የሚከናወን የመጀመሪያውን የቅድመ ውድድር ዝግጅት ፍልሚያ ከመስከረም 16 ጀምሮ እንደሚያደርግ መግለፁ ይታወቃል። በሀዋሳ ከተማ በሚካሄደው ውድድር ላይም የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ክለቦች እንደሚሳተፉ የታወቀ ሲሆን ውድድሩም አይነተኛ መልክ እንዲኖረው ሀገር በቀል የትጥቅ አምራች ተቋም ከሆነው ጎፈሬ ጋር ፌዴሬሽኑ በዛሬው ዕለት ይፋዊ የስያሜ መብት እና የአጋርነት ስምምነት ፈፅሟል።

ዛሬ ከሰዓት ቦሌ አካባቢ በሚገኘው በጎፈሬ ዋና ቢሮ በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የጎፈሬ መስራች እና ሥራ አስኪያጅ የሆኑት አቶ ሳሙኤል መኮንን ስለ ስምምነቱ አጠር ያለ ማብራሪያ ሰጥተዋል። ሥራ አስኪያጁ በንግግራቸውም ተቋማቸው የኢትዮጵያን እግርኳስ ለማሳደግ የተቋቋመ እንደሆነ አውስተው የፕሪምየር ሊግ ክለቦች ተካፋይ የሚሆኑበትን የሲዳማ ዋንጫ ውድድር በአጋርነት ለመስራት መስማማታቸውን ይፋ አድርገዋል። አቶ ሳሙኤል ጨምረው ውድድሩ የጎፈሬ የሲዳማ ዋንጫ በሚል ስያሜ እንደሚካሄድ ጠቁመው የተሳታፊ ክለቦችን ትጥቅ በነፃ እንደሚያቀርቡ አመላክተዋል። በተጨማሪም ውድድሩ የሚዲያ ሽፋን እንዲኖረው ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር የሚዲያ አጋር እንደሆኑ በስፍራው ለተገኙ የብዙሃን መገናኛ አባላት ተናግረዋል።

ከአቶ ሳሙኤል በመቀጠል መድረኩን የተረከቡት የሲዳማ እግርኳስ ፌዴሬሽን ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ አንበሴ አበበ ደግሞ ስምምነቱን እና ውድድሩን አስመልክቶ ተከታዩን ብለዋል።

“ለመጀመሪያ ጊዜ የሚደረገው ውድድር ልዩ መልክ እንዲኖረው እየጣርን ነው። ጎፈሬ ደግሞ ከእኛ ጋር እንዲሰራ ተስማምተናል። እርግጥ ስምምነቱ ለዚህ ውድድር ብቻ ሳይሆን ለቀጣይ ሦስት ዓመታት የሚዘልቅ ነው። በስምምነታችን መሰረት ጎፈሬ ለተሳታፊ ክለቦች የመወዳደሪያ ትጥቅ ያቀርባል። ለክለቦቹ ብቻ ሳይሆን ለዳኞችም ትጥቅ የሚያቀርብ ይሆናል። የዘንድሮው የመጀመሪያ ውድድራችን ቢሆንም በአቅማችን ጥሩ ስራዎችን ለመስራት እንሞክራለን። በቀጣይ ዓመት ደግሞ እያሻሻልን የምንሄድ ይሆናል።

“እኛ እንደ ክልል ፌዴሬሽን ውድድሩን ሰፋ አድርገን ለመጀመር አስበን ነው የተንቀሳቀስነው። እንደምታውቁት በክልሉ ሁለት ክለቦች ብቻ ናቸው በፕሪምየር ሊጉ የሚሳተፉት። ግን እኛ ሰፋ አድርገን ተጋባዦችንም በማምጣት ደማቅ ውድድር ለማድረግ ኮሚቴ አዋቅረን እየሰራን ነው። በውድድሩ ላይ የሚሳተፉ ክለቦች በሆቴልም ሆነ በመለማመጃ ሜዳ ላይ ምንም የሚቸግራቸው ነገር አይኖርም። እንደውም አንዳንዶቹ የቅድመ ውድድር ዝግጅታቸውን በከተማው ጀምረዋል። ስለዚህ ምንም የሚያሳስብ ነገር አይሆርም። ደማቅ ውድድር እንደሚኖረንም አስባለሁ።” ብለዋል።

ምክትል ፕሬዝዳንቱ ጨምረው በውድድሩ ሀዋሳ ከተማ፣ ሲዳማ ቡና፣ ሰበታ ከተማ፣ ጅማ አባጅፋር፣ ድሬዳዋ ከተማ፣ ሀዲያ ሆሳዕና፣ ኢትዮጵያ ቡና፣ ወልቂጤ ከተማ እና ወላይታ ዲቻ እንዲሳተፉ ጥያቄ ማቅረባቸውን አስታውሰው ኢትዮጵያ ቡና ሀሳብ በመቀየሩ፣ ወልቂጤ ከተማ እስካሁን ምላሽ ባለመስጠቱ እንዲሁም ወላይታ ድቻ እስከ ዛሬ ምሽት አሳውቃለው በማለቱ ቀሪዎቹ ስድስቱ ክለቦች ብቻ (ሀዋሳ፣ ሲዳማ፣ ሰበታ፣ ጅማ፣ ድሬዳዋ እና ሀዲያ) ማረጋገጫ መስጠታቸውን ተናግረዋል።

በሁለቱ አካላት ከተሰጠው ማብራሪያ በኋላ ደግሞ በስፍራው የተገኙ ጋዜጠኞች የተለያዩ ጥያቄዎችን አንስተው ምላሽ መሰጠት ተጀምሯል።

ስለ ስምምነቱ ይዘት?

“ይህ ስምምነት በዚህ ብቻ የሚቆም አይደለም። ውድድሩ እንዳለቀ የሚበተን አይደለም። በቀጣይ የሴቶች እግርኳስ ፣ የቅርጫት ኳስ እና የአትሌቲክስ ውድድሮችን ለማከናወን አስበናል። በዚህ ውድድር ጎፈሬ ስያሜውን ወስዷል። ሌላው ደግሞ እንደ ትጥቅ አቅራቢነቱ የውድድሩ ተሳታፊዎችን መለያ ያቀርባል። ውድድሩን ጎፈሬ እና የሲዳማ እግርኳስ ፌዴሬሽን ብቻ አይደለም የሚሰሩት። ሶከር ኢትዮጵያም የሚዲያ አጋራችን ነው። ስለዚህ ሦስታችን በትብብር የተሻለ ነገር ለመስራት እንሞክራለን።” አቶ ሳሙኤል መኮንን

“ጎፈሬ ከእግርኳስ ፌዴሬሽናችን ጋር በሲቲ ካፑ ውድድር ብቻ ነው ስምምነት የፈፀመው። ወደፊት ግን እግርኳስ ፌዴሬሽኑ እንደ ሲዳማ ሊግ አይነት ውድድሮችን ሲያደርግ በተመሳሳይ በአጋርነት የምንሰራ ይሆናል። ይህ ስምምነት ለሲቲ ካፑ ውድድር ብቻ ነው።” አቶ አንበሴ አበበ

በውድድሩ ላይ ስለሚኖሩ የተለዩ ነገሮች…?

“ጎፈሬ ዋናው ዓላማው በምስራቅ አፍሪካ ያለውን ነገር መቆጣጠር ነው። አሁን ግን በዚህ ውድድር ላይ ያሉ ነገሮችን እያየን ልምድ እናካብት ብለን ነው። በክልሉ ከሚገኙ ክለቦች ጋር ቀድመን ስምምነት ስለፈፀምን ነገሮች ቀለሉና ተስማምን እንጂ ወደፊት በሀገራችን አልፎም በምስራቅ አፍሪካ የሚኖሩ ሥራዎችን ለመስራት እንሞንራለን። በዚህ ውድድር ላይ የተለያዩ አዳዲስ ነገሮችን እንሞክራለን። እንዳልኩት የሚዲያ አጋር ይኖረናል። መረጃዎች ቶሎ ቶሎ እንዲደርሱ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ተስማምተናል። ከዚህ ውጪ በየጨዋታው የጨዋታ ኮከቦችን እንመርጣለን። ውድድሩ ሲቀርብ ደግሞ የሚኖሩ ሌሎች አዳዲስ ነገሮችን እንገልፃለን።” አቶ ሳሙኤል መኮንን

ስምምነቱ ወደ ገንዘብ ሲቀየር ምን ያህል ነው?

“በውድድሩ ጎፈሬ የራሱ ድርሻ አለው። ከማኔጅመንት ወጪ ያሉትን ወጪዎች ጎፈሬ ይሸፍናል። የተሳታፊ ክለቦች እና የዳኞችን ትጥቅ እንዳልነው እናቀርባለን። በዘንድሮ ውድድር አቅማችንን አሳይተን ከቀጣይ ዓመት ጀምሮ ደግሞ ከፌዴሬሽኑ ጋር በመነጋገር ውድድሩን ወደ ቢዝነስ ለመቀየር እንጥራለን። በአጠቃላይ ይህ ስምምነት ከ1.5 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የሚወጣበት ስምምነት ነው።” አቶ ሳሙኤል መኮንን

“በዚህ ስምምነት ለሲዳማ እግርኳስ ፌዴሬሽን የሚሰጥ ገንዘብ አይኖርም። ግን ጎፈሬ ወጪዎችን ይሸፍንልናል። ወደፊት አቅማቸውን እያየን ደግሞ ወደ ገንዘብ ስምምነት እናሳድገዋለን። የአሁኑ ስምምነት ጎፈሬ እና የሲዳማ እግርኳስ ፌዴሬሽን መተዋወቂያ ነው። በዚህ ትንሽ ውድድር የጎፈሬን አቅም እናይና ወደፊት በሚኖሩ ትላልቅ ውድድሮች ላይ ስምምነቱን እያሳደግን እንሄዳለን። ስለዚህ አሁን ገንዘብ ላይ ትኩረት አላደረግንም። አሁን ትኩረታችን ስራው ላይ ብቻ ነው።” አቶ አንበሴ አበበ

ደጋፊዎች በውድድሩ ወደ ስታዲየም ይገባሉ?

“አዎ ደጋፊዎች ስታዲየም ይገባሉ። የሲዳማ እግርኳስ ፌዴሬሽንም ደጋፊዎች ወደ ሜዳ የሚገቡበትን መንገድ ይሰራል። ከኮቪድ-19 ጋር በተያያዘም ስታዲየሙ ከሚችለው አቅም 1/4 ደጋፊ ወደ ሜዳ የሚገባ ይሆናል።” አቶ አንበሴ አበበ

በመጨረሻ አቶ ሳሙኤል መኮንን መስከረም 16 የሚጀምረው ውድድር የእጣ ማውጣት ሥነ-ስርዓት የፊታችን ሀሙስ በሀዋሳ ከተማ እንደሚካሄድ ገልፀው ሀሳባቸውን አገባደዋል። ከመግለጫው በኋላም ሁለቱ አካላት በይፋ ስምምነታቸውን ፈፅመዋል። ከስምምነቱ በኋላ ደግሞ ጎፈሬ ለሲዳማ እግርኳስ ፌዴሬሽን በስጦታ መልክ ትጥቅ አበርክቷል።