አዳማ ከተማ አዳዲስ አንበሎችን ሾሟል

ባለፈው የውድድር ዓመት ወጥ የሆነ አምበል ያልነበረው አዳማ ከተማ ለአዲስ የውድድር ዓመት ሦስት አንበሎችን መርጧል።

በአሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ በመመራት ለ2014 የውድድር ዘመን በአዳዲስ ተጫዋቾች ብቅ የሚለው አዳማ ከተማ ቡድኑን በአንበልነት የሚመሩ ሦስት ተጫዋቾችን መምረጣቸው ታውቋል።

በበርካታ ክለቦች እና በብሔራዊ ቡድን በመጫወት ከፍተኛ ልምድ ያለው ግብጠባቂው ጀማል ጣስው በአዳማም ተመራጭ አንበል ሆኗል። ግብ ጠባቂው በክረምቱ ቡድኑን የተቀላቀለ ሲሆን ባለፈው የውድድር ዓመት በወልቂጤ ከተማ አምበል ሆኖ ማሳለፉ ይታወሳል።

በሁለተኛነት አዳማ ከተማን ከተቀላቀለበት ያለፈው የውድድር ዘመን አጋማሽ ጀምሮ አንስቶ አንበል በመሆን ቡድኑን ያገለገው ኤልያስ ማሞ ሲደረግ ሌላኛው ወደ ቀድሞ ክለቡ ዳግም የተመለሰው ዳዋ ሆቴሳ ሦስተኛ አንበል እንዲሆን የተመረጠ ተጫዋች ነው።

በአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ በምድብ ለ ከቅዱስ ጊዮርጊስ፥ ባህር ዳር ከተማ እና ፋሲል ከነማ ጋር የተደለደለው አዳማ ከተማ ከቀናት በኃላ በውድድሩ ላይ የሚኖረውን አቋም የምንመለከት ይሆናል።